Friday, November 1, 2013

“ለሳቅ ባይተዋሩ” – ገጣሚ ፋሲል ተካልኝ ለኮሜዲያን አብርሃም አስመላሽ የቋጠረው ስንኝ


ታሞ..ታሞ..ታሞ..ታሞ
ሰው ድኖ ይታያል..ከሕመሙ አገግሞ::
ታሞ..ታሞ..ታሞ..ታሞ..
ሰው ይሞታል ደግሞ::
ለምን?..ለምን?..እኮ ለምን?..
ምነዋ ተገኘሁ?..መዳንህን ሳምን::
…ታሞ መሞት አለ!
ድንገት ወጥቶ መቅረት
…በአንተ አልተጀመረ::
የቆየ ሐቅ ነው..ያለ..የነበረ..
በዘመናት ብዛት..ለአፍታ እንኩዋ ያልተሻረ
ዛዲያ ለምን ልቤ?
ነባሩን ሐቁን ስቶ..
ሞትህን መቀበል..ማመን ተቸገረ::
አዲስ ሆኖ ዛሬ..የተለየው አንተ
ስንታለ የኖረ?!?..ሳይኖር እኮ የሞተ::
ሰው ሟች ፍጡር ነው..ድንገት ወጥቶ ቀሪ
በምድር ላይ ነግሶ..
ለካ ሞት ብቻ ነው..ሕያው ሆኖ ኗሪ::
ተዘልፍልፎ ሲታይ..
የተኛ ቢመስልም..ጣምኖና ደክሞት
ሲያዘናጋ ነው..
ከቶ አያንቀላፋም..ለካ አጅሬ ሞት!!
ድንገት ወጥቶ የቀረ.. ላይመጣ የሔደ
ቅኔ እንደተቀኘ..
“አንቱ” የተሰኘ..
ዘመኑን በሙሉ..ችሎ እንደኮመደ
ለሳቅ ባይተዋሩ..ሕይወትን ያሳቀ
ሕይወት ያደመቀ..
በኑሮው የነፈዘ..በኑሮው ያለቀሰ
ቅኔውን..ምፀቱን..
ቧልቱና ዘበቱን..ጀምሮ ያልጨረሰ
ተፈጥሮው የረቀቀ..በፈጠራው የላቀ
እንደማሾ በርቶ..
ብርሐን ለግሶ..ነዶ ነዶ ያለቀ
ሞት ላይ የቀለደ..ሞት ላይ የዘበተ
ሞትን ያሳቀቀ..ሞትን የገዘተ
ማናለ እንዳንተ?!?..
ቀልዶ የኖረ..ቀልዶ የሞተ::
* * *

No comments:

Post a Comment