Wednesday, April 17, 2013

ፓርቲዎች የተመደበላቸውን ሚዲያ በሚገባ አልተጠቀሙም | FANA

by Daniel Berhane on Thursday, April 18, 2013
ለአንድ ወር ያህል በተካሄደው የምረጡኝ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ ፣ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አጋር ድርጅቶች በተመደበላቸው የአየር ሰዓትና አምድ ሙሉ ለሙሉ አለመጠቀማቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብረ እንደተናገሩት፤ በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ተድልድሎላቸው የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ሲያካሂዱ ቢቆዩም ሙሉ ለሙሉ አልተጠቀሙበትም።
የአየር ሰዓት ድልድሉ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተዘጋጀው መመሪያ መሠረት የተከፋፈለ ሲሆን፤በዚህም ኢህአዴግ ከተመደበለት ሰዓት 70 በመቶ ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 50 በመቶ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች 36 በመቶ ተጠቅመዋል ።
«ለምርጫ ዘመቻው የተመደበው የአየር ሰዓት ወደ ብር ሲመነዘር ወደ 12 ሚሊዮን ብር ያወጣል» ያሉት አቶ ልዑል፤የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት በአግባቡ አለመጠቀማቸው እንደ ድክመት እንደሚታይ አብራርተዋል።
ይሁን እንጅ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድ እና የብሮድካስት ባለስልጣን ያወጡትን የምርጫ ቅስቀሳ ህግ በአግባቡ መተግበራቸው በስኬት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል።
በመጨረሻም መገናኛ ብዙኃን ለቅስቀሳው መሳካት እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘገባ ያመለክታል።
በሕጉ መሰረትም የምርጫ ቅስቀሳው ለአንድ ወር መካሄዱ ይታወሳል።
**********

No comments:

Post a Comment