Tuesday, April 2, 2013

በቤንሻንጉል ክልል የሰፈሩ ዜጐች “ሕገወጥ” በሚል ተባረሩ


Posted by From-Other-Media on Wednesday, April 3, 2013  ADDIS ADMASS

በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ በማጣታቸውና የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ ተዘዋውረው የከተሙ በርካታ ሰዎች በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ የያሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበል ዳኛ በበኩላቸው ‹‹ከየትኛውም ክልል የሚመጡ ሰዎች ለወረዳው ካላሳወቁና ካላስፈቀዱ ሕገወጥ በመሆናቸው ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ስምምነት ላይ ደርሰናል›› ብለዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት፤ ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ ይኖሩበት ከነበረው ክልል የመሸኛ ደብዳቤ አምጥተው በያሶ ወረዳና በየቀበሌዎቹ የነዋሪነት መታወቂያ ስለተሰጣቸው ጎጆ ቀልሰው ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በቅርቡ “ከሌላ ቦታ እየመጣችሁና እየሠራችሁ የአካባቢውን ተወላጅ ሰነፍ አደረጋችሁት” በሚል ምክኒያት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ሳይሰበስቡ ከክልሉ እንዲወጡ መደረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡ በያሶ ወረዳ ውስጥ የከተማ ነዋሪነትና የንግድ ፈቃድ በማውጣት ላለፉት ሰባት ዓመታት በሥራ ላይ መቆየታቸውን የሚናገሩት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ግለሰብ፤ መታወቂያቸውና ቀደም ሲል ይኖሩበት ከነበረው ክልል ያመጡት መሸኛ ደብዳቤ ተወስዶ እንደተቀደደባቸው፤ በከተማው የሠሩትን ቤት መላ እስኪያሲዙና ንብረታቸውን እስኪሰበስቡ ጊዜ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ‹‹ቤትና ንብረቱ የሚገባው ለወረዳው ነው›› በሚል ወረዳውን ለቀው እንዲወጡ በመገደዳቸው በከተማው አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ተደብቀው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን በያሶ ወረዳ ውስጥ በሀሎ ትክሻ፣ ሆኒ፣ ሊጐ፣ ባብርኮ፣ ሻብቲ፣ ድልድል፣ ቲኒጆ መጢና በመሰል ቀበሌዎች በግምት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ ከአማራ ክልል የመጡ ሰዎች እንደሚገኙ የገለፁት ግለሰቡ፤ እንደማንኛውም ዜጋ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ሠርቶ የመኖር መብታቸውን መሠረት አድርገው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተሻለ ሥራ ፍለጋ መሄዳቸውንና ሕገወጥ ሰፈራ አለማድረጋቸውን ገልፀው በደሉን እያደረሱባቸው ያሉት የወረዳው ባለሥልጣናት በመሆናቸው አቤት የሚሉበት ቦታ ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቤተሰባቸውን እና ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ ከየቀበሌው እየተያዙ በያሶ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የታሠሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሀሎ በተባለው ቀበሌ ነዋሪ እንደሆኑ የሚናገሩት ሌላው ግለሰብ እንደሚሉት፤ ከ1997 ጀምሮ የቀበሌው ነዋሪ በመሆን ከክልሉ ተወላጆች ጋር በስምምነት መሬት የእኩል እያረሱ የራሳቸውንም የባለመሬቱንም ሕይወት መቀየራቸውን ገልፀው፣ አሁን ግን ሕገ-ወጥ ናችሁ በሚል እንገልት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የክልሉ ነዋሪ ወዶንና ተቀብሎን በሰላም ነበር የምንኖረው” የሚሉት እኚህ አርሶ አደር የመኖሪያ ቤት ለመሥራት እንኳን የክልሉ ተወላጆች መሬት ቆርሰው እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ግን ጐጐታ በተባለ ቀበሌ ከአማራ ክልል የመጡ 43 ሰዎች እንዲሁም በሀሎ ሙከአርባ ቀበሌ የ25 ሰዎች መታወቂያ ተቀዳዶ ሲጣል መመልከታቸውን፣ ከተቀደዱት መታወቂያዎች አንዱ የእርሳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንደሚሉት የጉሙዝ ተወላጅ ከሆኑት ባለመሬቶች አንድ ገበሬ በጉልበቱ አርሶ 20 ኩንታል እህል ቢያመርት 10ሩን ለባለመሬቱ እኩል አካፍሎ በስምምነት ሲኖሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “እስከአሁን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ከታሠሩት በርካታ ሰዎች በተጨማሪ በመኪና ተጭነው ነቀምትና ጊንቢ የተወሰዱት ሰዎች ጉዳይ አስጨንቆናል” ያሉት ሌላው ግለሰብ ለታሠሩ ወገኖቻቸው ስንቅ ሊያቀብሉ የሚሄዱትም በዚያው እየተያዙ እንደሚታሠሩ ተናግረዋል፡፡
ስንቅ ሊያቀብሉ በመሄዳቸው ሦስት ቀን ታስረው እንደተለቀቁ የተናገሩት እኚህ ግለሰብ “ከክልላችን መሸኛ ደብዳቤ አምጥተን ሕገ-ወጥ ናችሁ የምንባለው ፓስፖርት ማውጣት ነበረብን?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹በኖርንባቸው ሰባትና ስምንት ዓመታት ሠርተን ለመለወጥ ከማሰብ በስተቀር በነዋሪውም ሆነ በአካባቢው ላይ ያደረስነው አንዳችም ችግር የለም” የሚሉት እኚህ ግለሰብ ‹‹ውጡ ከተባልንም ንብረታችንን እስክንሰበስብ ጊዜ ይሰጠን፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ቦታ ይሰጠን›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን የያሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበል ዳኛ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው፤ ከየትኛውም ክልል ሲመጡ ለወረዳው አሳውቀውና አስፈቅደው ካልሆነ ሕገወጥ በመሆናቸው ወደየመጡበት እንዲመለሱ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ታደሰ አክለውም፤ በአሁን ሰዓት ወደመጡበት እንዲመለሱ የተደረጉት ሕገወጥ የሆኑት እንጂ በሕጋዊ መንገድ የገቡት እንዳልሆኑ በመግለጽ ሕጋዊ የሚባሉት ከክልላቸው ከወንጀልና ከመንግሥት እዳ ነፃ ስለመሆናቸውና በምንም ጉዳይ ከክልሉ የማይፈለጉ መሆናቸውን የሚልጽ የመሸኛ ደብዳቤ የሚያመጡትን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት ግን ጫካ እያቆራረጡና ወረዳው ሳያውቅ የገቡ በመሆናቸው ለክልሉም ሆነ ለወረዳው ስጋት መሆናቸው ስለተረጋገጠ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ ሕጋዊ ያልሆኑት ወደየመጡበት እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መታወቂያውን በተመለከተ፤በየቀበሌው ካሉ “ኪራይ ሰብሳቢ” ሠራተኞች 500 ብር እየከፈሉ በሕገወጥ መንገድ መውሰዳቸው ስለተደረሰበት ጉዳዩ በጥብቅ እየተጣራ ነው፡፡
ተቀደደ ስለሚባለው መታወቂያና መሸኛ ግን ምንም መረጃ እንደሌላቸው የተናገሩት የወረዳው ዋና መስተዳድር በዚህ ረገድ ሪፖርት ያደረገ አንድም ሰው አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ተጣርቶ ሕገወጦች ወደመጡበት እንዲመለሱ የተወሰነው፤ በብአዴን፣ኦህዴድ እና የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ በኾነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ ፓርቲ (ቤጉብዴፓ) በጋራ ተወያይተው በደረሱበት ውሳኔ መኾኑን ሥራው የወረዳው ብቻ ሳይሆን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በትስስር እየተሠራ መኾኑን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ተመላሾቹ በሰላም ወደየመጡበት እንዲመለሱና እንግልት እንዳይደርስባቸው ከፍትህ አካላትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተመለሱ መሆናቸውን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ በያሶ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በርካታ እስረኞች አሉ መባሉን አስተባብለዋል፡፡
የዜጐች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን በተለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የሕግ ባለሞያ አቶ ግዛው ለገሠ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 32 “የመዘዋወር ነፃነት” በሚል ርእስ ስር ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመኖርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት መብት እንዳለው መደንገጉን ገልፀዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 41 ንዑስ ርእስ 1 ላይ “የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶች” በሚል ርእስ ስር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያ የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት እንዳለው የተቀመጠ ሲሆን ዜጐች በመላው አገሪቱ ሄደው የመሥራትና የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው አቶ ግዛው ለገሠ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ እንደ ሕግ ባለሞያው ገለፃ ሰዎች ከትውልድ ቦታቸው ሄደው በሚኖሩበት አካባቢ ጥፋት እንኳን ቢያጠፉ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል እንጂ ከሚኖሩበት ቦታ እንዲወጡ ሊደረግ እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡
**********
Source: Addis Admas – March 25, 2013. Originally titled “ለዓመታት ኑሯቸውን በቤንሻንጉል ክልል ያደረጉ ዜጐች ተባረሩ”

No comments:

Post a Comment