ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ዛሬ ሊነጋጋ ሲል ከ20 በላይ መኪኖች የፍኖተ-ሰላም ከተማን ማጨናነቃቸውን የተናገሩት ተፈናቃዮች፣ ከብር-ሸለቆ የመጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዞን እና ከወረዳ ፖሊስ አባላት ጋር በመተባበር፣ ተፈናቃዮቹ ወደ መኪኖቹ እንዲገቡ አዘዋል።
ጥሪው ድንገተኛ የሆነባቸው ተፈናቃዮች የሚያደርጉት ጥፍቷቸው ሲላቀሱ ፣ ወላጆቻቸውን ተከትሎም ህጻናት ሲያለቅሱ ይታዩ እንደነበር የአይን እማኞች ይናገራሉ።
አንድ ሌላ ተፈናቃይ ዛሬ ስላጋጠማቸው ነገር ሲናገሩ ” ሰው በተወለደበት አገር ይህን አይነት በደል ይደርስበታል” ብየ አላስብም ነበር ብለዋል።
ወደ መጣበት ቦታ ለመመለስ በመጠባበቅ ላይ የነበረ አንድ ወጣት ፣ ቤቱ መቃጠሉን ቢገልጽም መንግስት እንዳደረገ ያድርገን በማለት እንደሚሄድ ገልጿል።
ወደ መጣበት ቦታ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ ተፈናቃይ፣ ለምን እንደማይመለስ ሲጠየቅ ” በእርሱና በልጆቹ ላይ ለሚደርስበት ጉዳት ዋስትና ስላልተሰጠው” መሆኑን ገልጿል። የ2 ልጆች አባት መሆኑን የገለጸው አርሶአደሩ የልጆቹ እናት በህመም ምክንያት ራቅ ወዳለ ቦታ በመሄዷ፣ ልጆቹን ይዞ ለመመለስ አለመድፈሩን ተናግሯል።
በዛሬው እለት 16 መኪኖች ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ያቀኑ ሲሆን፣ በነገው እለትም ተጨማሪ ሰዎች ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተፈናቃዮች ስለሚያቀርቡት አቤቱታ የዞኑን የጸጥታ ሀላፊ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት ለማነጋገር ሳይቻል ቀርቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአማራ ተወላጆች ላይ የተወሰደውን እርምጃ በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፎችናንና የተለያዩ ዝግጅቶችን እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ስርክአዲስ ታየ ተጨማሪ ዘገባ ልካለች።
No comments:
Post a Comment