Thursday, January 31, 2013

ነፃ የወጣው የኦሮሞ ነፃ አውጪ

ቀስ በቀስ ደረጃ በደረጃ የሰከነ የሃሳብ እድገት፣ ብስለትና መረዳት ከዘመናት ለውጥ ጋር መሻሻልን መፍጠሩ እውነት ነው። ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማኖር፣ ይልቁንም ደግሞ በነፃነት ለመኖር ከወራሪዎች ጋር በተደረገ ትግል ሁሉ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሰዋል። ለዚህ ታሪክ ሥሪት የኦሮሞ ልጆች ያልከፈሉት መስዋዕትነት አልነበረም። ኢትዮጵያን ግብርና መራሽ ኢኮኖሚ እስከዛሬ ካቆያት ደግሞ ያለ ኦሮሞ ኢትዮጵያ የለችም። የዚያኑ ያህል ኢትዮጵያ ምሉዕ የምትሆነው ከየትኛውም ዘር ይፈጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ክብር፣ እኩል መብትና ነፃነት ሲኖረው ነው።
በአንድ የዘመን ቅንፍ ውስጥ የተፈጠሩ የስህተት መንገድን እውነት ብለው የተቀበሉ የኩረጃ ትውልዶች ስለነጻነት ያነበቡትና ስለመገንጠል ተገነዘብን ያሉትን አምጥተው የሀገራቸውን አመሰራረትና ታሪክ ሳይሆን የአውሮፓ ታሪክን ባዩበት ዐይን እንደ ሰው ያስከበራቸውን ኢትዮጵያዊነት ኮንነዋል።
አገር የፈጠሩ መስሎአቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስም ከጠላት በላይ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ ኢትዮጵያን ምስቅልቅል ያደረጋትና ሁሌም ከሁዋላ ቀሮች አንደኛ የሚያደርጋት አበሳዋ የበዛው በዚሁ መሰረታዊ የእውቀት ረሃብም ጭምር ነው።
በዘሩ ትምክህት የነበረውም፣ ተጎዳሁና ተናቅሁ የሚለውም የመረጡት መንገድ ሥህተት ነበር። ያንን ስህተት እየደገሙ መሄድ ወይም አለባብሰው የሚበጀን ይህ ነው ከማለት ጥፋት እንዳይደገም አድርጎ ለመሄድ መነሳት እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነገር ነው። የኦሮሞ ነፃ አውጪ ድርጅትም ለኢትዮጵያውያን አበሳ መብዛት ይልቁንም ደግሞ የኦሮሞ ልጆት ልብ ውስጥ በሌሎች ላይ ጥላቻን በመትከል፣ ክፋትን በመስበክ ለረዥም ዘመናት የቆየ ድርጅት በመሆኑ በርካቶች የመከራቸው ምንጭ ሌላው ብሄረሰብ እንደሆነ አድርገው እንዲቀበሉ አድርጎ ነበር።
ከዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት የተደረገው ትግል ግን የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም። ድርጅቱ ምን ያህል አስቸጋሪ ጉዞዎችን እንዳደረገና ከአጠገቡ ብዙ የትግል ጓዶችንም የሚያሳጣው እንደሆነ የሚጠራጠር አይኖርም። በተለይ የትግራይ ተገንጣይ ቡድን በኦሮሞ ልጆች ላይ ያደረሰው በደል ያስቆጣቸው ወጣቶች ድርጅቱ አሁን የመረጠውን መንገድ ለመቀበል ሊያስቸግራቸው እንደሚችልም መገመት አያዳግትም። ግን መደረግ የነበረበት ሆነና ድርጅቱ ለግማሽ ምዕተአመት ያነገበውን ‘በማነስ የማደግ’ ህልሙንበአንድነት ወደ መበልጸግ እውነት ቀይሮ በመምጣት ታላቅ ተግባር አከናወነ። ለዚች አገር ነፃነትና ክብር ያለፉትን የኦሮሞ ልጆች አፅም የክብር ቦታ፣ ለነብሳቸው ደግሞ ሀሤትን የሚሰጥ ውሳኔ መወሰኑ በእጅጉ የሚያስደስት ነው።
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ድርጅት እወክለዋለሁ ለሚለው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ለኢትዮጵያ ፖለቲካም ትልቅ አስተምህሮት ያለው ድርጊትን ነው የፈጸመው። ከትናንቱ ተምሮና ትምክህትን ዋጥ አድርጎ እውነታውን ተቀብሎ መንገድ የማስተካከልን ትምህርት ለሁሉም አበርክቶአልና ሊመሰገን ይገባዋል። ባለ ሁለት ፀጉር የፖለቲካ ድርጅቶች የመማር አቅማቸው ካልከዳቸው ከዚህ እውቀትና ልምድ ሊቀስሙ እንደሚችሉ የታመነ ነው። በየወሩ የሚፈለፈሉትም የፖለቲካ ድርጅቶችም በመጀመርያ መደራደርና መቻቻልን ቢማሩ ወደ ድል የሚወስደው ጎዳና አጭር እንደሚሆን ከዚሁ ክስተት ሊማሩ ይችላሉ። የኦሮሞ ነፃ አውጪ ድርጅት አሁን ከያዘው ስሙ በስተቀር የተቀበለው አቋም ወደ ኢትዮጵያ ነፃ አውጪነት እንደሚያሸጋግረው ተስፋ የሚያስጥልም ነው።
የኢትዮጵያን ፖለቲካና አስተዳደር ለመቅረጽ ከፈረንጅ የምንገለብጠውን ነገር ቀነስ አድርገን ከአለም ተሞክሮዎች ሁሉ በመማር የራሳችንን መንገድ ለመንደፍ አዕምሮአችን የሚተጋ ቢሆን ደግሞ የበለጠ አስተማማኝ መንገድ ልንመርጥ እንችላለን። አውርዱልኝ (Readymade)  ከመግዛት በልክ ማሰፋት የበለጠ መሆኑን ማን ያጣው ይሆን?
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የወል ስምን ምስጢር እንደተነተነው ‘ወል’ ማለት የጋራ አብሮነት እንደሆነው ሁሉ የጋራ አገራችንን ወል አሶፍኔ (ተነጋግረን)፣ወል መሪአኔ (ተመካክረንና)፣ወል ሆጄኔ (አብረን ሰርተን) የኦሮሞ ልጆች የሚከበሩባትንና የሚኮሩባትን ከሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ጋር በጋራ የሚኖሩባትን፤ ከጠበበ የጎጥ እሳቤ ወደ ገዘፈው አገራዊ ግንዛቤ የሚያሸጋግረንን መንገድ መምረጥ ወደ ነፃነታችን ቀረብ ያደርገናልና ‘ኢጆሌ ቢየ-አባኮ ጀባዳ’ እንላለን።  ለፊደላችን ብልጽግናና ለቋንቋችን ውበት የኦሮሞ ጠበብቶች እውቀትም ፈሶበታልና ልዩነት ለማስፋት ባህር ማዶ መሄዱንም በማስተዋል እናርመው ይሆናል የሚል ተስፋም አለን።
በመጀመርያ አስሮ ከሚይዘን የተሳሳተ ሃሳብ ነፃ መውጣት የትክክለኛ ጎዳና ግማሽ መንገድ ላይ መድረስ ይሆናል። የኦሮሞ ነፃ አውጪ ድርጅት ካሰረው ጎጠኛነት ኢትዮጵያዊነቱን ወድዶና ፈቅዶ አገኘው እናም ነፃ ወጣ። ጨቆኑኝ የሚላቸው ሁሉ በዚህ ሲደሰቱ አክርሮ ሲታገላቸው የኖሩት አቅፈው እየሳሙት ወዳጁ ሆኑ። በፍቅር ማሸነፍም ይኸው ነው። የቀረው በዘር ነፃነት ሳቢያ አገር አንቆ የሚገድለውን የትግራይ ተገንጣይ ማንበርከክ ይሆናል።
ነፃ የወጣውን የኦሮሞ ነፃ አውጪ ከዚህ ታሪካዊ ጎዳና ላይ ያደረሱት ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል። ኦሮሞነት ደግነት ነው፣ ኦሮሞነት ፍቅር ነው፣ ኦሮሞነት ታታሪነት ነው ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ በሁሉም ልጆችዋ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች።


No comments:

Post a Comment