Thursday, January 31, 2013


“የመበስበሱ በሽታ ሁሉም ዘንድ ነው”

ሻዕቢያው በረከት ህወሃትን ሊነዱት ይሆን?
bereket vs sebhat


የአቶ በረከት ስምዖንና የአቶ ስብሃት ነጋ የደፈጣ ውጊያ ገሃድ መውጣቱን የሚያመላክት መረጃ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በህወሃት መንደር ውስጥ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሯል። ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት ልዩነቱን ለማርገብ በከፍተኛ ደረጃ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም።
ከፍተኛ ስልጣን የያዙትንና አቶ መለስ ለመተካካት ያዘጋጇቸውን አዳዲስ አመራሮች፣ በቅርቡ ደንብና ህግ በመጣስ ሹመት የሰጡዋቸውን ጨምሮ የሰራዊቱን አዛዦችና ደህንነቱን ከጎናቸው ያሳተፉት ክፍሎች የተፈጠረው ልዩነት እልባት ማግኘት ይገባዋል የሚል አቋም መያዛቸውን የሚጠቁሙ ክፍሎች እነማን ተለይተው እንደሚመቱ ለመገመት አስቸጋሪ መሆኑንን ይገልጻሉ።
“ፓርቲያችን ከእንጥሉ በስብሷል” በማለት ከዛሬ አስራአንድ ዓመት በፊት በአገር ክህደት ሊያስወግዷቸው የተነሱትን ጓዶቻቸውን የረቱት መለስ የተጠቀሙበት ዋንኛ ስልት አባይ ጸሃዬን “ከውህዳኑ” ጋር በማሰለፍ ነበር። ዛሬ ለህወሃትና ለትግራይ ህዝብ በትግርኛ ቋንቋ ተጽፎ ተሰራጨ የተባለውና ይህንኑ መረጃ ዋቢ በማድረግ ኢየሩሳሌም አርአያ በተለያዩ ድረገጾች ይፋ እንዳደረጉት አቶ አባይ ጸሐዬ የተመደቡት ወጥመዱ ከተጠመደባቸው ዘንድ ነው።
“ድርጅትህ ኢህአዴግ እስከዛሬ ታግሎ እዚህ አድርሶሃል። በተለይም የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ የሆነው ባለ ራዕዩን መሪህን በቅርቡ አጥተሃል” የሚል የአምልኮ መሪ ቃል ያለበት የጥሪ ወረቀት “ተቆርቋሪ ለሆናችሁ የትግራይ ተወላጆች በሙሉ” በማለት ጥሪ አቅርቧል። ኢየሩሳሌም አርአያ ቃል በቃል በትምህርተ ጥቅስ አኑረው ባሰራጩት በዚህ ጉልህ ዜና “እነ አቶ በረከት፣ ወ/ሮ አዜብ፣ ቴዎድሮስ ሃጎስ” ወረቀቱን አዘጋጅተው እንዳሰራጩ ያስረዳል።
በኢየሩሳሌም አርአያ ዜና ላይ እንደተመለከተው እነ አቶ ስዩም መስፍን፣ አባይ ጸሐዬ፣ አለቃ ጸጋዬ ከነባለቤታቸው የትግራይን ህዝብ ለጠላት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ያወሳል።  “… የኔ የምትላቸው ጅቦች ተነስተውብህ ይገኛሉ” የተጠቀሱትንና ሌሎች ደጋፊዎቻቸውን “ጅቦች” ሲል የሚጠራው መልዕክት፣ “… ከእኛ ኋላ የተፈጠሩና ራሳችን ያሳደግናቸው ሲጠናከሩ ድርጅታችን ግን እየተዳከመ በመሄድ ላይ ነው” ሲል ያሳስባል። እነማን እንደሆኑ በግልጽ ሳይዘረዘር “የተወገዱ ግን በመጥፎ ጎዳና ያልተሰማሩን መልሰን ወደ ፓርቲው ማስገባት አለብን። ይህ ካልሆነ ግን የህዝብ ትግል አውላላ ሜዳ ላይ ጅብ በልቶት ሊቀር ነው ከጠላቶቻችን ጋር እንታረቅ እያሉን ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ ያስቀምጣል። በስተመጨረሻ  “ከጀርባ ሆኖ የዚህ አፍራሽ ዋና ቀያሽ መሃንዲስ ስብሃት ነጋ መሆኑን ደርሰንበታል” ይላል።
“የኢህአዴግ ስኬት የመስመር እንጂ የግለሰብ አይደለም” በማለት የመለስን አምልኮ ለመቃወም ቀዳሚ የሆኑት አቶ ስብሃት ኤፈርትን ለወ/ሮ አዜብ ካስረከቡ በኋላ ከድርጅቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ መሆኑን ለማሳየት እንደ ሩቅ ተመልካች አስተያየት ሲሰጡ ባብዛኛው ባልተለመደ መልክ ይዛለፉ ነበር። በተለይም አቶ በረከትን የማኮሰስና ምናምንቴ አድርጎ የማሳየት ስልት ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ አለመግባባቱ ሊከሰት ግድ እንደሆነ አስቀድመው የተነበዩም ነበሩ።
“… መለስ ስለሌሉ የወንበር ቡቅሻው የማይቀር ነው። በድርጅቱ አመራሮች ዘንድ የሌባና ፖሊስ፣ የሃይል ሚዛንና ቅኝት፣ አሰላለፍን የማሳመር ሰልፍ እየታየ ነው፤ … የመለስ ማለፍ በድርጅቱ ውስጥ ታፍኖ የቆየውን ቁርሾ ማፈንዳቱ አይቀርም…” ሲሉ ኦክቶበር 25 ቀን 2012 ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ቃለ ምልልስ የሰጡት አሁን በትምህርት ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ ሰው፣ የኢህአዴግ ድልድይ ተሰብሯል፤ የጋራ ነጥብም የለውም ብለው ነበር።
አውራምባ ታይምስ በበኩሉ ምንጩን አዲስ አበባ በማለት በተመሳሳይ የህወሃትን አደጋ ውስጥ መውደቅ ሲያበስር በስም ከዘረዘራቸው አመራሮች መካከል አቶ ስብሃት ነጋን አልጠቀሰም። ኢየሩሳሌም አርአያ አቶ በረከት የሚዘውሩትና የእነ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ወገን በዋናነት ለመምታት ያሰበው አቶ ስብሃት ነጋን እንደሆነ ለአባላት ተበተነ የተባለውን የማስጠንቀቂያ ወረቀት በመጥቀስ ይገልጻል።
አውራምባ ታይምስ “እያጣራሁ አቀርበዋለሁ” በማለት ያወጣው ትኩስ ዜና ለህወሃት አባላት ተሰራጨ የተባለውን ደብዳቤ “ማን እንደጻፈው አልታወቀም” በማለት ብዥታ የሚያጭር መልክት ሲያስተላልፍ፣ ኢየሩሳሌም አርአያ ከአውራምባ ድረገጽ ባለቤት አቶ ዳዊት ከበደ በተለየ መልኩ ዜናውን በትነው አስረድተዋል። በሁሉም በኩል እንደተጠቀሰው ህወሃት ቀውስ ውስጥ ተነክሯል።
በየካቲት ወር በሚደረግ ድርጅታዊ ግምገማ ጠራርገው እንደሚያስወግዷቸው እንደ ከባድ ሚዛን ቦክስ ቀጠሮ በመያዝ እነ አቶ ስብሃት፣ ስዩም፣ አባይና አለቃ ጸጋዬን በመጥቀስ የተሰራጨው  ወረቀት በስተመጨረሻ ስብሃት ነጋ ላይ ክርኑን አስደቁሶ እንደሚያበቃ የህዋሃትን ጓዳ አስመልክቶ በተደጋጋሚ ለየት ያለ ዜና የሚያስነብቡት ኢየሩሳሌም አርአያ ያበቃሉ።
ጎልጉል ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው የነበሩት የኢህአዴግ ሰው ይህንን ዜና አስመልክተው ምን አስተያየት እንዳላቸው ጠይቀናቸው ነበር። “በሌሎቹም አቻ ድርጅቶች ውስጥ በተመሳሳይ ይህ ሁኔታ ይከሰታል። የመበስበሱ በሽታ ሁሉም ዘንድ ነው” በማለት መልሳቸውን ይጀምራሉ። ለጊዜው ደኢህዴንና ብአዴን አንድ ላይ መሆናቸውን ያስታወቁት እኚሁ አስተያየት ሰጪ የኦህዴድ አቋም አለመጥራቱን ነው የሚናገሩት።
“የድጋፉ ጉዳይ የፎርሙላ ነው። ዶ/ር ደብረጽዮንና በረከት ስለላውን፣ ጦር ሃይሉን፣ የፖሊስና የልዩ ሃይሉን ሙሉ በሙሉ ስለተቆጣጠሩት በአሸናፊነት እንደሚወጡ ጥርጥር የለውም” ካሉ በኋላ አቶ ስብሃት ሰሞኑን “አማራውን ከሰደብኩ እኔ ታምሜያለሁ ማለት ነው ሆስፒታል መሔድ አለብኘኝ” በማለት የሰጡት መግለጫ ሲዘልፉትና ሲረግሙት የኖሩትን አማራና ብአዴንን ተለሳልሶ ለመቅረብ ያደረጉት እንደሆነ በተዋረድ ለብአዴን አባሎች መገለጹን እንደሚያውቁ አስረድተዋል።
“ምንም ተባለ ምን በመከላከያውና በደህንነቱ ሃይል ተጠቅመው የፈለጉትን መወሰንና የማስወሰን፣ ባላቸው በሚሰራው የፖለቲካ መዋቅር እስከታች መመሪያ በማውረድ የእነ በረከት ወገን ባለድል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ቀድሞ ታጋይ የነበሩ፣ የደህንነት ሃይሉን እየረዱ ብር የሚያመርቱ ግርግሩ ስለማይመቻቸው ሃይል ካለው ወገን ጋር በመሆናቸው እነ ስብሃትን ያቀላጥፏቸዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግለሂስ አድርገው አርፈው ለመቀመጥ ካልተስማሙ ብቻ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ይደመድማሉ፡፡
ይህንን መረጃ በሚያጠናክር መልኩ ከዚህ በፊት ከጻፍናቸው ዜናዎች መካከል አቶ በረከትና አቶ ሃይለማርያም የመለስ የቅርብ ሰዎች መሆናቸውንና አቶ መለስ ወደ ውጪ ሲወጡ የሥልጣኑን ቁልፍ የሚሰጡት ለአቶ በረከት እንደሆነ፤ የአቶ ሃይለማርያም ሹመት መነሻውም በዚሁ ቀደም ሲል በተፈጠረ “የቤተሰብ መሰል” ግንኙነት መሆኑን በመናገር ስማቸው ሳይጠቀስ ቃላቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የሰጡ የኦህዴድ ሰው ጠቅሰን መጻፋችን የሚታወስ ነው፡፡ አቶ መለስ በሞቱ ማግስት ከኢህአዴግ ምክርቤት እና ከፓርላማው ውሳኔ በፊት አቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚ/ር ሆነው እንደሚቀጥሉ በመናገር የተጠባባቂ ጠ/ሚ/ርነት ሥልጣን ይዘው እንደሚሠሩ አቶ በረከት በወቅቱ በሰጡት ቃለምልልስ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም ለፎርማሊቲ በፓርላማ ፊት ቀርበው ምህላ እንደሚፈጽሙ አቶ በረከት በግላቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይህንኑ ቤተሰባዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን መዘገባችን የሚጠቀስ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment