ምንአልባትም የዛሬው ድርጅታቸው ኢህአዴግ አርቆ አሳቢነት የፈጠረው ይሁን ወይም ሌላ፣ ድንገት የሬድዋንን ፓርቲ የሚቃወም አዲስ ፓርቲ ብቅ አለ፣ በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሚኒስትር በሆኑት ሲራጅ ፈርጌሳ አማካኝነት ይመራ የነበረው ይህ ፓርቲ የስልጤ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ስሕዴድ) ይሰኛል፡፡ … እሾን በእሾህ፣ ፓርቲን በፓርቲ፡፡ እናም የሬድዋን ትግል ከኢህአዴግ ጋር ብቻ መሆኑ ቀርቶ ከሌላኛው የስልጤ ህዝብ ድርጅት ጋርም ሆነ፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከልም የከረረ የውክልና ፉክክር ተፈጠረ፡ ፡ በሽግግር መንግስቱ ዘመን ‹‹የኦሮሞን ህዝብ በትክክል የምወክለው እኔ ነኝ›› በሚል በኦነግ እና በኦህዴድ መካከል የነበረው ፉክክር አይነት ወራቤ ላይም ተደገመ፡፡ ቃላቶችን እያሰካኩ ያለማቋረጥ የመናገር ተሰጥኦ ያላቸው ሬድዋንም በአገኙት አጋጣሚ በሲራጅ ፈርጌሳ የሚመራውን ስሕዴድ ‹‹የኢህአዴግ ተላላኪ፣ ተለጣፊ፣ አሻንጉሊት…›› እያሉ ይተቹት እንደነበር የትላንት ትውስታ ነው፡፡ ትውስታችንንም በማስረጃ ለማስደገፍ ያህል ሬድዋን የተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር በነበሩበት ዘመን በ1993 ዓ.ም. ታህሳስ ወር ከታተመው ከጎህ መጽሔት ጋር ከአደረጉት ቃለ መጠይቅ ጥቂቱን እንቀንጭብ፡፡ መጽሔቱም የሳቸውን ድርጅት የማይደግፉ የስልጤ ተወላጆች መኖራቸውን ጠቅሶ ይኼ ከምን የመነጨ እንደሆነ እንዲያብራሩለት ጠየቃቸው፡፡ ሬድዋንም ሲመልሱ እንዲህ አሉ፡- ‹‹…የስልጤን ብሔረሰብ በተለያየ ስያሜ ፈርጀው የተንቀሳቀሱት የብሔረሰቡ ተወላጆች የኋላ ኋላ እውነቱን ቢረዱም ጥቅም ፍለጋ በዚያው ሰክረው ቀሩ እንጂ የተፈጠረው ምስቅልቅል በመጀመሪያ የራሱ የሆኑ መነሻዎች አሉት፡፡›› ሬድዋን ወደ ኢህአዴግ ያዘነበሉትን የስልጤ ተወላጆችን ነው ‹‹ጥቅም ፍለጋ በዚያው ሰክረው ቀሩ›› ሲሉ የወነጅሉት፡፡ በዛ በደጉ ዘመን፡፡ በእርግጥ ዛሬ ሬድዋን እንዲህ ሊሉ አይችሉ፡፡
በብራሃን ፍጥነት ራሳቸውም ከዋነኞቹ ኢህአዴጎች አንዱ ሆነዋልና፡፡ ሆኖም ሬድዋን ከኢህአዴግ ተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግ አመራርነት የተሸጋገሩበት ምክንያት ‹‹ጥቅም ፍለጋ በዚያው ሰክረው ቀሩ›› ሲሉ የወነጀሏቸውን ሰዎች ፈለግ ተከትለው ይሁን ወይም የግንባሩ ፖለቲካ አዋጭነት ገብቷቸው ከሳቸው ሌላ የሚያውቅ የለም፡፡
ምንጭ. ባባአ አየዱ
No comments:
Post a Comment