Saturday, August 2, 2014

የሴት ልጅ ግርዛትን የመቀነስ ፈተና

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተላለፉት ዜናዎች ቀልቤን የሳበው በእንግሊዝ ሎንዶን እየተላለፈ ያለው ስብሰባ (Girls Summit 2014) ነው፡፡ በዜናው እንደተገለጸው የሴት ልጅ ግርዛት እንደዲቆም ያለመው ይህ ስብሰባ
የተወሰኑ አገሮች መሪዎችን፣ መንግሥታዊና የግል ድርጅት ተወካዮችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ሰዎችን ያሳተፈ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ በሴት ልጅ ግርዛት ስፋት በአንደኝነት ከተፈረጁት ውስጥ ሶማሊያ (98%)፣ ጊኒ (97%) ሲገኙበት በሁለተኛ ደረጃ እንደ ጂቡቲ (93%)፣ ግብፅ (91%) ይገኙበታል፡፡ ዘገባው በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጣቸው ኤርትራ (83%) እንዲሁም ሱዳን (88%) አገሮችን ነው፡፡ የኢትዮጵያን በተመለከተ ዘገባው ስፋቱ ምን ያህል እንደሆነ ሳይገልጽ በመቀነስ ደረጃ ለውጥ ካመጡ አገሮች መካከል እነደሆነች ገለጸ፡፡ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ካልሆነ በቀር አገራችን የሴት ልጅ ግርዛት ከተንሰራፋባቸው አገሮች መካከል የተመደበች ሲሆን ስፋቱም 74% እንደሆነ በዚሁ ስብሰባ የወጣው የዩኒሴፍ ሪፖርት አሳይቷል፡፡ ይህ አሃዝ አገራችን የሴት ልጅ ግርዛትን በመቀነስ ረገድ አጠንክራ እንድትሠራ ከሚያደርግ በቀር በምንም መስፈርት ሊያኩራራት ወይም በጣም እንደሠራች በኩራት ልትናገርበት የምትችልበት አይደለም፡፡

የሴት ልጅ ግርዛት (Female Genital Mutilation (or cutting) ማለት በባህል፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ ምክንያት የሴት ልጅ ብልት የተለያዩ አካላት የሚቆረጡበት ልማድ ነው፡፡ ዓይነቱና አፈጻጸሙ ብዙ ሲሆን በሴቷ ላይ የተለያዩ የጤና ጉዳቶችን የሚያስከትል ልማድ ነው፡፡ አስከፊነቱን ለመረዳት የድርጊቱን አፈጻጸም ማሰብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከሴቷ መብት አንፃር የሴት ልጅ ግርዛት የሴቷን የአካል ደኅንነት፣ የግላዊነት፣ የትምህርት፣ የጤና ወዘተ. መብቶችን የሚጥስ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍና ብሔራዊ ሕግጋት በወንጀልነት የተፈረጀና የሚያስቀጣ ነው፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት ሰፊ ውግዘት ቢደርስበትም ለዘመናት በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጸምና ብዙ ሴቶችን ለሞት፣ ለስቃይና ለተለያዩ የጤና መታወኮች የሚዳርግ ነው፡፡ በዚህ ሰሞን በሎንዶን የተደረገው ጉባዔ የሴት ልጅ ግርዛትን ከትውልዱ ለማስወገድ ጠንካራ ሥራዎች መሠራት እንዳለበት ተሳታፊዎች የተስማሙበት ሲሆን፣ አገራችንም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯና በሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ተወክላ አቋሟንና ዕቅዷን ገልጻለች፡፡ በዚህ ጽሑፍ በጉባዔው የተገለጹ መረጃዎችን፣ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ፣ ዕቅዷንና ተግዳሮቶችን በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡ 
እንግሊዝም እንደ እኛ
የሴት ልጅ ግርዛት አፍሪካና እስያን በመሰሉ ያላደጉ አገሮች መስፋት አስገራሚ አይደለም፡፡ እነዚህ አገሮች የባህልና ሃይማኖት ምክንያት ይህን ጎጅ ልማድ ለዘመናት ሲፈጽሙት የቆዩት ሃቅ ነው፡፡ ገራሚው ችግሩ ያደጉትም አገሮች መሆኑን ስንሰማ ነው፡፡ በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ችግሩ በአገራቸው እየሰፋ መምጣቱን ካሰመሩበት በኋላ የሴት ልጅ ግርዛት ከዚህ ትውልድ እንዳያልፍ ጠንካራ ሥራዎች ይጠብቁናል ብለዋል፡፡ እንግሊዝ ጎጅ ልማዱን ለማስቀረት የተለየ ተዓምር የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገሮች የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቆም መሥራት አለባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራቸው ያሉ ወላጆች ልጆቻቸው ግርዛትን እንዳይፈጽሙ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን የወንጀል ክስ እንደሚቀርብባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስከ 137,000 የሚደርሱ በእንግሊዝና በዌልስ የሚገኙ ሴቶች ግርዛት አከናውነዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1985 ጀምሮ ግርዛት በእንግሊዝ ወንጀል ቢሆንም አሁን በሒደት ላይ ካሉ የተወሰኑ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ውጭ እስካሁን የተቀጣ የለም፡፡ እንግሊዝ ጎጅ ልማዱን ለመቀነስ የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ለችግር የተጋለጡትን ለመከላከልና የተጠቁትን ለመንከባከብ በዓመት 1.4 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መድባለች፡፡ 
ጉባዔውን ከእንግሊዝ ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው ዩኒሴፍ ግን ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እንደ ዩኒሴፍ ገለጻ ባለፉት 30 ዓመታት የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ መቀነሱ ቢታመንም፣ አገሮች ጠንካራ ዕርምጃ ካልወሰዱ ባላደጉ አገሮች ላይ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ዕድገት ጥረቱን መና እንዳያስቀረው ሥጋት አለ፡፡ እንደ ዩኒሴፍ መረጃ የሴት ልጅ ግርዛት በተለመደበት በ29 የአፍሪካና የእስያ አገሮች ቁጥራቸው ከ130 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ልጃገረዶችና ሴቶች የሴት ልጅ ግርዛት አከናውነዋል፡፡ ከ700,000 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ደግሞ ያለዕድሜያቸው ተድረዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ዩኒሴፍ አገሮች የሚወስዱት ዕርምጃ ካልተጠናከረ የሴቶችን ሕይወት በዘለቄታው የሚጎዳው፣ ሴቶች የራሳቸውን ውሳኔ እንዳይሰጡና እምቅ ችሎታቸውን እንዳይጠቀሙ የሚያደርገው የሴት ልጅ ግርዛት ለማስወገድ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡
የአገራችን ነገርስ?
አገራችን የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ በስፋት ከሚገኝባቸው አገሮች ቀዳሚ ተርታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ጎጅ ልማዱን ለማስቀረት አገራችን በ1996 ዓ.ም. በወጣው የወንጀል ሕጓ ግርዛትን ጨምሮ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በወንጀልነት እንደሚያስቀጡ ደንግጋለች፡፡ ሕጉ ከወጣም በኋላ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግርዛትን ለመቀነስ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርፀው ቢንቀሳቀሱም በስፋቱ ላይ ያመጡት ለውጥ አመርቂ አይደለም፡፡ ችግሩ ሳይጠፋ ከመገናኛ ብዙኃን የጠፋው አጀንዳ ቢኖር የሴት ልጅ ግርዛት ነው፡፡ በአገራችን በባህልና በሃይማኖት ምክንያት የሚፈጸም የሴት ልጅ ግርዛት ሰፊ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ ልማዱ በመፈጸም ላይ ነው፡፡ ድርጊቱ የሚፈጸመው በድብቅ፣ ለጤና ጎጅ በሆኑ መሣሪያዎችና በሃይማኖትና ባህል ምክንያት በመሆኑ ግርዛትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት አሰልች አድርጎታል፡፡ ግርዛትን የተመለከተ ብሔራዊ መረጃ የሚገኘው እ.ኤ.አ. በ2011 በተሠራው የሕዝብና የጤና ዳሰሳ (Demographic and Health Survey) ላይ ነው፡፡ በዚህ ዳሰሳ መሠረት 23 በመቶ የሚሆኑ ከ14 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በብሔራዊ ደረጃ ግርዛትን ፈጽመዋል፡፡ የክልላዊ ሥርዓቱን ከተመለከትን የተለያዩ አሃዞች የሚታዩ ሲሆን፣ ዝቅተኛ ከሆነው የጋምቤላ ክልል 7 በመቶ እስከ ከፍተኛው የአፋር ክልል ድረስ 60 በመቶ ሥርጭቱ አለ፡፡ ከአፋር ቀጥሎ አማራና ሶማሌ ክልሎች እንደ ቅደም ተከተላቸው በ47% እና 31 በመቶ የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት የሚገኝባቸው ክልሎች ናቸው፡፡ ይህ መረጃ ከ15 ዓመት በታች ያሉትን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ ከዚህ የዕድሜ ክልል በላይ የሚፈጸም ግርዛት በስፋት መገኘቱ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡
በሎንዶን በተደረገው ጉባዔ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ የገለጹት ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ከ14 ዓመት በታች የሚፈጸም የሴት ልጅ ግርዛት እ.ኤ.አ. በ2000 ከነበረበት 52 በመቶ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ 23 በመቶ የቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም የሕፃናት ያለዕድሜ ጋብቻ ከ33.1 በመቶ (1997) ወደ 21.4 በመቶ (2010) መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሯ በዚህ ስኬት የሚኮሩ መሆናቸውን በመግለጽ ሌሎች አገሮች የኢትዮጵያን ተምሳሌት መውሰድ የሚችሉ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ከ14 ዓመት በላይ የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ ያለው ስፋት በጉባዔው ያልተገለጸ ሲሆን፣ ዩኒሴፍ ይፋ ያደረገው መረጃ ግን የሴት ልጅ ግርዛት (ከ15 እስከ 49 ዓመት) ስፋት በአገራችን 74 በመቶ መድረሱን አመልክቷል፡፡ ተከታዩን መረጃ ይመለከቷል፡፡
አገራችን የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የምትችልበት ዓመት 2025 እንደሆነ በጉባዔው የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ ሴቶችን ከጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመጠበቅ ወሳኙ ትምህርት መሆኑን በማስመር ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሴቶች በትምህርት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከትምህርት ውጭ 38,000 የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች መሰማራታቸው የሴት ልጅ ግርዛትን ለማቆም እንደሚያስችል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች መካከል ለማሰለፍ ዕቅድ በተያዘበት 2025 የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቀረት ሴቶችን ማዕከል ካደረገው የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣመ መሆኑ በጉባዔው ተገልጿል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማስፈጸም ያመች ዘንድ ኢትዮጵያ አራት ተከታታይና ተያያዥ ዘዴዎችን መቅረጿ በጉባዔው ተመልክቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 በሚደረገው የሕዝብና የጤና ዳሰሳ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማወቅ የሚያስችሉ መስፈርቶችን ማካተት፣ ጎጅ ልማዱን ለማስቀረት ከሚሠሩ ብሔራዊ መዋቅሮች ጋር ማቀናጀት፣ ጠንካራና ተጠያቂነት ያለው የሕግ አፈጻጸም ዘዴዎችን ማጠናከር እንዲሁም አሁን ከሚያዘው በጀት 10 በመቶ መጨመር አቅጣጫዎቹ ናቸው፡፡
ተግዳሮቶች
የሴት ልጅ ግርዛትን በ2025 ማስቀረት ትልቅ ግብ ቢሆንም መፈጸሙ በተግዳሮቶች የተሞላ ነው፡፡ ግቡን ለመፈጸም የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸው የማይካድ ነው፡፡ የሴት ልጅ ግርዛትን ወንጀል የሚያደርግና የሚቀጣ የወንጀል ሕግ መኖሩ፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ማዕከል ያደረጉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት መዋቅር ሥራ ላይ መዋሉ፣ እስካሁን የተሠሩትና የተጀመሩት ግርዛትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች መኖራቸው፣ መንግሥት ስትራቴጂ በመንደፍና በጀቱን በአሥር በመቶ ለመጨመር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳየቱ እንደ መልካም ዕድል መወሰድ የሚችሉ ስኬቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ተግዳሮቶችን ለመወጣት የሚያስችል ዝግጅትም ካልታሰበበት ግርዛትን ማስቀረት ዕቅድ ሳይሆን ህልም እንዳይሆን ሥጋት አለ፡፡ የተወሰኑ ተግዳሮቶችን ለመጠቆም እንሞክር፡፡
በቂ ጥናት አለመኖሩ
የሴት ልጅ ግርዛት ስፋትን የተመለከተ ወቅታዊ ጥናት አለመኖሩ የችግሩን ስፋትና መፍትሔውን ለማቀድ አያስችልም፡፡ በብዛት የሚታዩት ጥናቶች ከሌሎች ልማዳዊ ድርጊቶች (ከጠለፋ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ወዘተ.) ጋር የተቀላቀሉና በአብዛኛው መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥናቶች ያልተቀናጁና ብሔራዊ ባልሆኑ መጠን የሴት ልጅ ግርዛት ያለበትን ደረጃ ስፋቱን፣ ዓይነቶቹንና የአፈጻጸሙ መነሻ ምክንያትን ለማወቅ አያስችልም፡፡ ከዚህ አንፃር አገራችን የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያሳይ ብሔራዊ የዳሰሳ ጥናት /Base line survey/ ልታዘጋጅ ያስፈልጋል፡፡ ጥናቱ ለስትራቴጂው ማስፈጸሚያ፣ ለሕዝብ ቅስቀሳና የሕግ አፈጻጸሙን ለማጠናከር መነሻ ይሆናል፡፡
አመክንዮ የመመርመር ሥራ
የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቆም አስቸጋሪ የሚሆነው ኅብረተሰቡ ድርጊቱን ለመፈጸም የባህልና የሃይማኖት አመክንዮ ስለሚያቀርብ ነው፡፡ የባህል ምክንያትን የአገር ሽማግሌዎችን ግንዛቤ በመጨመር፣ ሴቶቹን በማስተማር እንዲሁም ጎጅ ባህሉን በመልካም ባህል መቀየር ይቻላል፡፡ የሃይማኖት አመክንዮ ግን ትልቅ ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ በአገራችን የሴት ልጅ ግርዛት የተንሰራፋባቸው የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የመፈጸሙ አመክንዮ ሃይማኖት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የኅብረተሰቡ እምነት የሆነው እስልምና የሴት ልጅ ግርዛትን እንደሚከለክል በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ቀርበው ሐሳባቸውን የገለጹ የሃይማኖት አባቶች መኖራቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ አንፃር የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት የሚታቀድ ዕቅድ የሃይማኖት አባቶችንም ያካተተ መሆን ስለሚገባው፣ የሃይማኖት አባቶችን አሠልጥኖ በቂ ግንዛቤ ከፈጠሩ በኋላ ሃይማኖቱ ባለው አደረጃጀት ኅብረተሰቡ ግንዛቤው እንዲጨምር ማድረግ ተገቢ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ 
የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መቀዝቀዝ
አገራችን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅን ካፀደቀች በኋላ በመብት ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴ መዳከሙ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አገራችን ከአዋጁ በፊት አስመዝግቤዋለሁ የምትለው የሴት ልጅ ግርዛትን የሚቀጣ የወንጀል ሕግ ማዘጋጀት፣ ኅብረተሰቡና የሕግ አስፈጻሚ አካላት በጎጂ ልማዱ ላይ ያላቸው ግንዛቤ መጨመር የተቻለው በሲቪክ ማኅበራቱ ተሳትፎ ነው፡፡ የአዋጁ ከልካይ ድንጋጌዎች ማኅበራቱ በግርዛት ላይ እንደ ቀድሞው እንዲሠሩ ባያስችልም የሚያሠራ የሕግ ድንጋጌዎችም እንዳሉትም መገንዘብ ይገባል፡፡ በመንግሥትና በሲቪክ ማኅበራቱ መካከል በሚደረግ ስምምነት ሲቪክ ማኅበራቱ ከውጭ በሚያገኙት በጀት የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ሊሠሩ የሚችሉበት የሕግ አግባብ አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ በመብት ላይ የሚሠሩ የአገር ውስጥ የሲቪክ ማኅበራት ከአውሮፓ ኅብረት ወይም ዓለም ባንክ ለተወሰኑ ፕሮጀክቶች የሚያገኙት በጀት እንደ አገር ውስጥ በጀት ተቆጥሮ እንደሚሠሩት ዓይነት ተሞክሮ በሴት ልጅ ግርዛት ላይም ቢተገበር መንግሥት ያሰበውን ዕቅድ ለማስፈጸም ይችላል፡፡ ሲቪክ ማኅበራቱ በሴት ልጅ ግርዛት ላይ ያላቸው ልምድ፣ የአድቮኪሲ ዘዴ፣ ባላቸው ኔትወርክ የሌሎች አገሮችን ልምድ ለማምጣት መቻላቸው መንግሥት እንዲጠቀምባቸው ያስገድዳል፡፡ መንግሥት ኔትዎርክ በመፍጠር ግርዛትን ለማስቀረት ስትራቴጂ መንደፉን ለማስፈጸም የሲቪክ ማኅበራቱን አቅም መገንባትና የሚያሠራ ሥርዓት መፍጠር ግድ ይለዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ዝምታ
መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አራተኛ አካል (The fourth branch of a government) የሆኑትን ያህል የመንግሥትን ተጠያቂነት ለመገምገም፣ ሕዝብን ለማስተማርና ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለመዘገብ ብቁ ተቋማት ናቸው፡፡ የሴት ልጅ ግርዛትን በማስቀረት ረገድ መገናኛ ብዙኃን ያላቸው ሚና ሰፊ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ በኋላ በዚህ ረገድ ዝምታ ረብቦባቸዋል፡፡ ቀድሞ ስለ ግርዛት አስከፊነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመሆኑ፣ የግለሰቦች ታሪክን በመዘገብ፣ በፍርድ ቤት የተቀጡትን ለሕዝብ በማሳወቅ ይሳተፉ የነበሩት የመገናኛ ብዙኃን አሁን እንደ ድሮው ሲጽፉ፣ ሲናገሩ፣ ሲያሳዩ አይስተዋልም፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት በ2025 የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ሲያቅድ መገናኛ ብዙኃን ዋና ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን በመገንዘብ የሚዲያ ስትራቴጂ ነድፎ ሊያሳትፋቸው ይገባል፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ እንደምናስተውለው መገናኛ ብዙኃን ኅብረተሰብ ተኮር የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮችን በመዳሰስና በመዘገብ የሚያመጡት ለውጥ አመርቂ ነው፡፡ በአገራችንም  ከዓረብ አገሮች ስደት፣ ስቃይና ጉዞ ጋር በተያያዘ መገናኛ ብዙኃን የነበራቸው ትልቅ ድርሻ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ሎንዶን በተደረገው ጉባዔ አገራችን እስከ 2025 የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ቃል መግባቷ መንግሥት የሚያስመሰግነው ነው፡፡ አሁን ያለንበት የ74 በመቶ ከ15 እስከ 49 ዓመት ያሉ ሴቶች የግርዛት ስፋት ብዙ መሥራት እንደሚገባን የሚያሳይ እንጂ የሚያኩራራን አይደለም፡፡ ችግሩ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እንደመሆኑ መጠን ለአፍታም ችላ ሊባል የሚገባው አይደለም፡፡ ችግሩ እንኳን የእኛ የምዕራባውያንም የራስ ምታት መሆኑ ከእንግሊዝ ልምድ መማር እንችላለን፡፡ ግርዛቱ ቢቆም ከሴቶቹ እኩል አገራችን ተጠቃሚ መሆኗ ለሁሉም ለመረዳት የማያስቸግር ሃቅ ነው፡፡ ሴቶቹ ጤነኛ ከሆኑ ጤናማ ቤተሰብ፣ የተማረ ወጣት፣ ብቁና ለአገር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንስት ቁጥር ይበዛል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት የገባው ቃል መልካም ቢሆንም የነደፋቸውን መርሃ ግብሮች ለማስፈጸም ያሉትን ብሔራዊ መልካም አጋጣሚዎች ከመጠቀም ጎን ለጎን ያሉበትን ተግዳሮቶች ለይቶ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በቂ መረጃ መሰብሰብ፣ ኅብረተሰቡ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ አመክንዮችን መርምሮ መፍትሔ መቅረፅ፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በጥምረት መሥራት ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ 2025 ሲመጣ ኅብረተሰባችን ከሴት ልጅ ግርዛት የፀዳ ይሆንን? ነገ የምንመለከተው ይሆናል፡፡ 
source  http://www.ethiopianreporter.com/



No comments:

Post a Comment