Tuesday, January 7, 2014

በኢትዮጵያ የአደገኛ እጾች ተጠቃሚ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው ተባለ

ታህሳስ ፳፰( ሃያ ስምንት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአደገኛ እጾች ተጠቃሚ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በህጻናት እና በሴቶች ላይ የሚደረሰውም ጉዳት ጨምሯል።
የተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት ሰንደቅ ጋዜጣ በስፋት ዘግቦታል።
በኢትዮጵያ በሶስት አመታት ውስጥ ብቻ 543 439 ኪሎ ግራም ወይም 5 434 ኩንታል  ካናቢስ 208 172 ወይም 2 8 መቶ ከንታል ኮኬይን፣ 409 ኪሎግራም ሄሮይን እና 6 300 ኪሎ ግራም አምፌታሚን የተባለ አደገኛ ዕጽ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ የሚዘዋወረው የካናቢስና የሌሎች እጾች መጠን በፖሊስ ቊጥጥር ስር ከዋለው በብዙ እጅ  እንደሚልቅ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ካናቢስ በማምረት አደገኛ ተብለው የተፈረጁት ቦታዎች ኦሮምያ፣ ደቡብ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ናቸው። በኦሮምያ በሻሸመኔ አካባቢ 2 840 ካሬ ሜትር በላይ የካናቢስ ተክል ተገኝቷል።
በአደገኛ እጾች የተጠቁት ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሲሆኑ፣ ፖሊስ እንደሚለው ወጣቶቹ ወደዚህ ወንጀል የሚገቡት እጾቹ የሚያመጡትን ጉዳት ባለማወቅ፣ በጓደኞች ግፊት፣ እጾችንና መድሀኒቶችን በቀላሉ በማግኘት ነው። የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መጨመር፣ ከስራ እና ከትምህርት ቤት ውጭ ወጣቶች የሚያሳልፉባቸው የመዝናኛ ቦታዎች በብዛት አለመኖር ወጣቶችን ለአደገኛ ሱሶች እንደሚዳርጋቸው ጥናቶች ያሳያሉ።
አንዳንድ የፖሊስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአደገኛ እጾች ዝውውር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ጸጥታ አስከባሪዎች እና የመንግስ ባለስልጣናት ይገኙበታል።
በሌላ ዜና ደግሞ በሴቶችና በወንድ ህጻናትና ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ወሲባዊ ጥቃት ጨምሯል። ከሶስት አመት በፊት 520 ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት 14 በመቶ የሚሆኑት በህይወት ዘመናቸው አስገድዶ መድፈር አጋጥሞአቸዋል። 26 በመቶው የመደፈር መኩራ፣ 25 በመቶው በአስገድዶ መድፈር ለአልተፈለገ እርግዝና ተዳርገዋል።
በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ ህጻናትና ወጣቶች ላይ እየተፈጸመ  ያለው የወሲብ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱንም መረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮጵያን ጆርናል ኦፍ ሄልዝ ዴቨሎፕመንት የተባለው መጽሄት ባወጣው ሪፖርት ለወንድ ህጻናትና ወጣቶች መደፈር በምክንያትነት የቀረቡት ብስለት ማጣት፣ የወሲብ ፊልሞችን የማየት አጋጣሚ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የእጽ ተጠቃሚነት፣ የመጠላያ እጥረትና የጎዳና ላይ ህይወት መብዛት እንዲሁም ውስን የህግ ከለላ የሚሉት ይገኙበታል። ሀብታሞችና አዛውንቶች በጎዳና ተዳዳሪ ወንድ ህጻናት ላይ ጥቃት በማድረስ ግንባር ቀደም መሆናቸው በጥናቱ ተጠቅሷል።

በጥናቱ አስደንጋጭ ሆነ የቀረበው ፖሊሶችና ሌሎች ባለሙያዎች በጥቃቱ ተሳታፊ መሆናቸው እንዲሁም የምርመራው ሂደት ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተጽእኖ ማድረጋቸው  የሚለው ከፍል ነው። አንድ የፖሊስ መኮንን  ” በጉዳዩ ጥቂት ደረጃ ላይ እንደደረስክ ርቀህ እንዳትሄድ በአንዳንድ ሃላፊዎች ትከለካላለህ። ከተወሰነ ደረጃ በሁዋላም ክትትል እንድታቆም ትታዘዛለህሲል ለአጥኚዎች ተናግሯል።

No comments:

Post a Comment