Wednesday, January 8, 2014

‹‹ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሳካት የሚረዱ ሦስት የውጭ ኩባንያዎች የጠላት ሰለባ ሊሆኑ ነበር›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

‹‹ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሳካት የሚረዱ ሦስት የውጭ ኩባንያዎች የጠላት ሰለባ ሊሆኑ ነበር››  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
የአገሪቱን የዕድገትና ትራንስፌርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብለው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተመርጠው የገቡ ሦስት የውጭ ኩባንያዎች ላይ፣ ‹‹ጠላት ጥፋት ሊፈጽምባቸው እንደነበር ደርሰንበታል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ባለፈው ቅዳሜ ታኅሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው፡፡
‹‹ጠላት›› በተባለው አደጋ ሊደርስባቸው ነበር የተባሉት ሦስቱ የውጭ ኩባንያዎች የቱርኩ አይካ አዲስ፣ የሆላንዱ ሼር ኢትዮጵያና የቻይናው ሁንጂያን የጫማ አምራች ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ‹‹የጠላት የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ነበር፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም ይህንን የጥቃት ጉዳይ ያነሱት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ለመብታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢንዱስትሪዎችንም ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነት እንዳለባቸውና አንዳንድ ሠራተኞችም በእኩይ ተግባር ላይ ሊሰማሩ እንደሚችሉ በመጠቆም ነው፡፡
ጥቃት ሊፈጸምባቸው ነበር ስላሉዋቸው ኩባንያዎች ጉዳይ ሲገልጹም፣ ‹‹እነዚህ ሦስት ኩባንያዎችን በአንድ ሳምንት በተመሳሳይ ቀን የገጠማቸውን ልንገራችሁ፡፡ የዕድገታችን ጠላት ይህንን መንግሥት ማሽመድመድ የሚቻለው እነዚህን ሦስት ድርጅቶች በመምታት ነው ብሎ አቅዶ በድርጅቶቹ ውስጥ በመሠረተው ሴል አማካይነት ለአንድ ቀን እንዲጨናነቁ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡
እነዚህ ሦስት የኢንዱስትሪ ዘርፎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ሊፈጠሩ የሚችሉባቸው እንደሆኑ ያስታወቁት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ነገር ግን የሚገኘውን ዕድገትና አገርን ለመጉዳት የሚፈልግ ኃይል እነዚህ ድርጅቶች እንዲታወኩ ለማድረግ መሞከሩን አስረድተዋል፡፡
ይህ የተደረገው ደግሞ በሠራተኞች መካከል በሚገኙ እኩይ ተግባር በሚፈጽሙ ሴሎች አማካይነት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ስለጉዳዩ ዝርዝር ውስጥ እንደማይገቡ የገለጹት አቶ ኃይለ ማርርያም፣ ‹‹ጠላት›› ብለው የገለጹት አካልን ማንነት ግን አላብራሩም፡፡
‹‹ሙከራው ከሽፏል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ሲደረግ ግን መንግሥት ፖሊስ ማቆም ስለነበረበት ይህንን አድርጓል፡፡ እንዲህ ሲሆን ፖሊስ ጣልቃ ገባ ትላላችሁ፡፡ እዚህ ላይ ጣልቃ ካልገባ ሥራው ምን ሊሆን ነው?›› በማለት በወቅቱ የተፈጸመው የፖሊስ ጣልቃ ገብነት ትክክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተፈጠረ የተባለው ችግርም መፈታቱን ገልጸው፣ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ሠራተኛው በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
አንዳንድ ነገሮችን የሠራተኛ መሪዎች ካልተገነዘቡዋቸው ችግር ሊሆኑ እንደሚችሉ በማብራራት፣ ‹‹እኩይ ተግባር ውስጥ የሚገቡ የሠራተኛ መሪዎች ጭምር እንዳሉ በመገንዘብ፣ እነዚህን ጥቂት ግን ሁከታቸው ትልቅ የሆነና በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉትን በጋራ በመሆን ለመታገል ቃል ኪዳን መግባት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ያልተገቡ ክስተቶች ሲያጋጥሙ የጋራ ሥራ እንደሚጠይቅና የድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑትን ደግሞ በጋራ ማስወገድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹እንዲህ ባለው ድርጊት ለመሳተፍ በመሯሯጥ የሠራተኛ ማኅበር መሪ ለመሆን የሚፈልገውን ተባብረን ማስወገድ ይገባል፤›› ብለው፣ አብዛኛው [99 በመቶው] ጥሩ ቢሆንም አንድ በመቶ የሚሆነው ሲያጋጥም ድርጊቱን በጋራ መታገል እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹ሳይታሰብ በሚወሰድ ዕርምጃ የእኔ አመራር ተነካ ብለን የምንጮህ ከሆነ በኋላ መመለሻው ያጥረናል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እናንተ የማታውቁት እኛ በተጨባጭ የምናውቀው ነገር አለ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እነዚህ አካላት ከማን ጋር እንደሚገናኙና ምን ዓይነት ሴል እንዳላቸውም እናውቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲከሰቱ ከመንግሥትና ከሠራተኛ ማኅበራት አመራሮች ጋር በቅርብ መሥራቱ ከስህተት እንደሚያድን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ በሠራተኛው፣ በመንግሥትና በአሠሪው መካከል ያለውን ጉድለት በማስተካከል ለዕድገት መሥራቱ ጠቃሚ መሆኑንም አቶ ኃይለ ማርያም አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ በሠራተኛ ማኅበራት መሪዎችና በመንግሥት መካከል የተደረገው ውይይት ከሠራተኞች ለቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የተሰጠበት ነበር፡፡ ከ30 በላይ ጥያቄዎች ቀርበው መንግሥት ጥያቄዎቹን መርምሮ ለሁሉም ወገን ይበጃል የተባለ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎችም የመንግሥት ምላሽ እጅግ ያስደሰታቸውና ያልጠበቁት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽንም በተለይ በሠራተኞች የመደራጀት ጉዳይ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የራሱን ጥረት እንደሚያደርግና በጋራ ለመሥራትም ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ መድረኩ በጋራ ለመሥራት የሚያነሳሳ ጭምር ነበር ብሏል፡፡ በዕለቱ የተነሱ ጥያቄዎችንና ከመንግሥት ምላሽ የተሰጠባቸውን የተወሰኑ ጉዳዮች በገጽ 11 ላይ ይመልከቱ፡፡

No comments:

Post a Comment