Saturday, January 4, 2014

የኢንጂነር ጀሚል ሀሰን ጉዳዮች በድጋሚ ተፈረደባቸው

  •                                                                              Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
የሀዋሳ ጠ/ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የስንብት ደብዳቤ ደረሳቸው  ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በእስልምና ሀይማኖት በየወህረ የሚከበረውን “ሊቃ” የተሰኘ ሀይማኖታዊ በዓል ለመካፈል ወደ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ሚኬኤሎ ገበሬ ማህበር መልካሜ መሰጊድ የሄዱትና በእነ አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስና አጋሮቻቸው በድንጋይ ተቀጥቅጠው የሞቱት የኢ/ር ጀሚል ገዳዮች በደቡብ ክልል ሀዋሳ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በድጋሚ ተፈረደባቸው፡፡ የሀዋሳ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታረቀኝ አበራም ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ የስንብት ደብዳቤ እንደደረሳቸው ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ግንቦት 19 ቀን 2004 ዓ.ም በአካባቢው “የሀይማኖት መሪ” እየተባለ የሚጠራው አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ነገ ከአዲስ አበባ የሚመጡና የሊቃ በዓላችንን ሊያበላሹ የተዘጋጁ ሰዎች አሉ ሲመጡ በዱላ ደብድባችሁ ደሉ በሚል ባስተላለፈው ትዕዛዝ ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በበዓሉ ላይ የተገኙት ኢ/ር ጀሚል ሀሰን በድብደባው ህይወታቸው ሲያልፍ በበርካቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የቡታጅራ እና አካባቢው ከፍተኛ ፍ/ቤት ህዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም የግድያው ዋና መሪ፣ አዘጋጅና አዛዥ እንዲሁም የግድያው ቀድሞ ጀማሪዎች ናቸው በተባሉት በአቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፣ በወንድማቸው ነሲቡ ሰይድ ፋሪስ፣ በወልዩ ቦንሱሞ እና በሁሴን አብደላ ላይ በሶስት ተደራራቢ ወንጀሎች መስርቶ በግድያው ጠንሳሽና በወንድሙ ላይ የ14 እና የ19 ዓመት ፍርድ ያሳለፈ ሲሆን በሌሎች 20 ተባባሪዎች ላይ እንደየጥፋታቸው መጠን ከስምንት እስከ 11 ዓመት ፈርዶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በውሳኔው ቅር የተሰኘው የቡታጅራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሆሳዕና ምድብ ችሎት ይግባኝ ሲል ወንጀለኞቹ በበኩላቸው ሀዋሳ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ብለው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በጠ/ፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት በአቶ ታረቀኝ አበራ የተመራው ችሎት የወንጀለኞቹን ይግባኝ በደንብ መርምሮ ካየ በኋላ የአቃቤ ህግን ይግባኝ መዝገብ ከሆሳዕና በማስመጣትና በማጣመር ወንጀለኞቹን በተለይም የግድያውን ሂደት ጠንስሰዋል፣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ባላቸው ወንድማማቾች አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ እና በነሲቡ ሰይድ ሰልማን ላይ የ14 እና የ19 ዓመት ፍርዳቸውን አቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ አላቀረበም በሚል ወደ አምስት እና ወደ ዘጠኝ አመት ዝቅ ያደረገ ሲሆን የግድያው ተባባሪ ናቸው ያላቸውን ቀሪዎቹን ፍርድ ወደ አንድ አመት ከስምንት ወር ዝቅ በማድረግ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በእስር ቤት የቆዩበትን በማስላት በነፃ ያሰናበታቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ ውሳኔ እንባ ሲያፈሱ የነበሩት የሟች ቤተሰቦችና አቃቤ ህግ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳይ እንዲታይ ይግባኝ ያሉ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለወራት ያህል ከመረመረ በኋላ በነፃ የተለቀቁት ወንጀለኞች ሊለቀቁ አይገባም በሚል በሬዲዮና በጋዜጣ ያስጠራ ሲሆን ወንጀለኖቹ በመሰወራቸው ሊቀርቡ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህን ጉዳይ በጥልቀት ሲመረምር የቆየው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አምስት ዳኞችን ከሰየመ በኋላ ባለፈው ማክሰኞ ባዋለው ችሎት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የቀለለውን ቅጣት በቡታጅራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍርድ የበለጠ በሆነ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
የግድያ ወንጀሉን ጠንስሰዋል መርተዋል ባላቸው አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሽ ወንድማማቾች በአቶ ስልማን ሰይድ ፋሪስ ላይ የ18 ዓመት እስራት ሲፈርድ ግድያውን በማስጀመርና በጭካኔና ነውረኝነት በተሞላበት ሁኔታ ኢ/ር ጀሚልን ከደበደበ በኋላ በላያቸው ላይ ትልቅ ድንጋይ ጭኖባቸው ሄዷል ባለው በአቶ ነሲቡ ሰይድ ፋሪስ ላይ የ19 አመት ከ6 ወር እስራት መፍረዱ ታውቋል፡፡ ቀሪዎቹ የተሰዎሩት ሰዎች እና የግድያው ተባባሪ ናቸው ሆን ብለው ንብረት አውድመዋል በተባሉት 14 ሰዎች ላይ በሌሉበት የ16 ዓመት እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢንጂነር ጀሚልን ግድያ የይግባኝ ጉዳይ በደቡብ ክልል ጠ/ፍር ደቤት ሲመሩ የነበሩትና የወንጀለኞቹን የ14 እና የ19 አመት ቅጣትና የ11 አመት ቅጣት ወደ አምስት አመት እና ወደ ዘጠኝ አመት የቀሪዎቹን ደግሞ ወደ አንድ አመት ከስምንት ወር በማቅለል እንዲለቀቁ ያደረጉት እንዲሁም የደቡብ ክልል ቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታረቀኝ አበራ ትምህርት እንዲማር በሚል ሰበብ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የስንብት ደብዳቤ እንደደረሳቸው የአዲስ አድማስ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
የቡታ ጅራ ማረሚያ ተቋም ሃላፊ ኮሚንደር ወንድወሰን አበባም ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን እነዚሁ ምንጮች ገልፀውልናል፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2006 በወጣው እትማችን ላይ የኢንጂነር ጀሚልን የግድያ ሁኔታ የፍርድ ቤት ሂደትና የቡታጅራና አካባቢው ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔን፣ የይግባኙን ሂደትና ውሳኔዎችን በተለከተ ሃዋሳ በመሄድ የጠቅላይ ፍ/ቤቱን ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አበራን፣ የሃዋሳ ፍትህ ቢሮ ሃላፊዎችን የቡታጅራ ማረሚያ ተቋም ሃላፊ ኮማንደር ወንደሰን አበበን፣ የቡታጅራና አካባቢው ነዋሪዎችን እንዲሁም የሟች ቤተሰቦችን አናግረን ሰፊ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment