Saturday, February 1, 2014

ትራፊክ ጥሶ ለመሄድ በሞከረ ሚኒባስ ላይ በተተኮሱ ጥይቶች ሦስት ሰዎች ተጎዱ

ባለፈው ሐሙስ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ በተሳፋሪዎች ተሞልቶ ደሴ ሊጓዝ ነበር የተባለ አንድ ሚኒባስ፣ ለትራፊክ ዝግ የሆነ መንገድ ጥሶ ለማለፍ ሲሞክር በፀጥታ አስከባሪዎች በተተኮሱ ጥይቶች ሦስት ሰዎች መጎዳታቻውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ጥር 22 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጀመረውን የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ምክንያት በማድረግ፣ በተለያዩ ሰዓታት መሪዎቹ የሚተላለፉባቸው መንገዶች ለተወሰነ ጊዜ ለትራፊክ ዝግ የሚደረጉ መሆኑ ቢታወቅም፣ ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ ሊወጣ እንደነበር የተገለጸው ኮድ 3 የሆነና ለከተማ ትራንስፖርት ድጋፍ ከሚሰጡ ሚኒባሶች አንዱ የሆነው ተሽከርካሪ ሾፌር፣ ለምን ትራፊክ ጥሶ ለማለፍ እንደፈለገ በቁጥጥር ሥር ውሎ በምርመራ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሚኒባሱ ከካዛንቺስ ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ ከፊት በር ሁለት መቶ ሜትር በላይ አለፍ ብሎ ከፓርላማ መቶ ሜትር ያህል ዝቅ ብሎ በሚገኘው የታላቁ ቤተ መንግሥት መግቢያ በር አካባቢ በፀጥታ አስከባሪዎች ተኩስ ሊቆም ቢችልም፣ ከተሳፋሪዎቹ መካከል ባልና ሚስትን ጨምሮ ሌላ አንድ ግለሰብ በመቁሰላቸው፣ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ባጋጠመው ድንገተኛ ሁኔታ የሞቱም ሆነ በከባድ ሁኔታ የተጎዱ ተሳፋሪዎች ባይኖሩም፣ በወቅቱ በሚኒባሱ ውስጥ የነበሩት ተሳፋሪዎች በድንጋጤ ራሳቸውን ስተው እንደነበሩ በሥፍራው የተገኙ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የሚኒባሱ አሽከርካሪ መንገዱ ለትራፊክ ዝግ መሆኑን እያወቀ ጥሶ ለማለፍ የፈለገበትን ምክንያትና በምርምራ ወቅት የተገኘ ሌላ ምክንያት ካለ፣ እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸዋል ስለተባሉት ሦስት ግለሰቦች ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የፌደራል ፖሊስን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት፣ ‹‹ጉዳዩ በምርመራ ላይ ስለሆነ ምንም ማለት አንችልም›› በሚል ምላሽ ሊሳካ አልቻለም፡፡
ከወራት በፊት ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚደረጉ የሕዝብ ትራንስፖርት ጉዞዎች መታገዳቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ቁጥጥሩ በመላላቱ ምክንያት ጉዞዎች እንዳልተገቱ እየተነገረ ነው፡፡
source:www.ethiopianreporter

No comments:

Post a Comment