Wednesday, February 26, 2014

ሚኒስትሯ ግብረሰዶማዊነትን ደግፈዋል በሚል የተሰራጨውን መረጃ አስተባበሉ

W/ro Zenebu Tadesse
W/ro Zenebu Tadesse
የኢትዮጵያ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ የኡጋንዳ መንግስት በግብረሰዶማውያን ላይ ያወጣውን ሕግ እንደተቃወሙ ተደርጎ በግል የቲውተር ገፃቸው ላይ የሰፈረውን መረጃ አላውቀውም ሲሉ በሚኒስትር መ/ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በኩል አስተባበሉ።
ሚኒስትሯ በግል የቲውተር ገፃቸው አሰራጩት በተባለው አጭር መልዕክት ላይ የኡጋንዳ መንግስት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ የተሰማሩ ዜጎችን እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ቅጣት መቅጣቱን መቃወማቸውንና በግብረሰዶማዊነት ላይ መንግስት ሕግ የማውጣት ኃላፊነት እንደሌለበት የሚጠቁም መልዕክት እንዳስተላለፉ ተደርጎ ቀርቧል።
ሚኒስትሯ መልዕክቱን ያስተላለፉት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በግብረሰዶማዊነት ላይ ጠንካራ ሕግ በፊርማቸው ማፅደቃቸውን ተከትሎ ነው። የሚኒስትሯም አቋም በኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ዓለም አቀፍ ውግዘት መቀላቀላቸውን የሚያመለክት እንደሆነም ተገልጿል። የሚኒስትሯን አቋም የኡጋንዳ የግብረሰዶማውየን መብት ታጋይ ፍራንክ ሙጊሻ አወድሰዋል።

የወ/ሮ ዘነቡ የግል አስተያየት በቲውተር ገፃቸው ከወጣ በኋላ የግብረሰዶማውያን መብት ታጋዩ በቀጣይ ሕጉን ለመቃወም የሚደረገውን ትግል እንደሚያግዝ አያይዘው ተናግረዋል። ሌላኛው የደቡብ አፍሪካ የግብረሰዶማውያን መብት ተቆርቋሪ የሚኒስትሯ አስተያየትን ጠቃሚ በማለት አወድሰዋል። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮችም የወ/ሮ ዘነቡን ፈር መከተል ያለባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
የደቡብ አፍሪካው የግብረሰዶማውያኑ መብት ተከራካሪ ሜላኒ ናትሐን ጨምረው እንደገለፁት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የተከበረበት የደቡብ አፍሪካ መሪ ጃኮብ ዙማ ዝምታን በመረጡበት ሁኔታ ኢትዮጵያዊቷ ሚኒስትር በሕጉ ላይ በድፍረት መናገራቸውን በአድናቆት ገልፀውትም ነበር።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሕግ ያላት ሲሆን፤ በዚህ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ ሰው እስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣ መሆኑንም ይታወቃል።
የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የፀረ-ግብረሰዶማውየንን ሕግ በፊርማቸው ካፀደቁ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት እየገጠማቸው ነው። ፕሬዝዳንቱን ካወገዙት መካከል የደቡብ አፍሪካው የኖቤል ሽልማት አሸናፊው ቄስ ዴዝሞን ቱቱ ይገኙበታል። ቄስ ቱቱ የኡጋንዳውን የፀረ-ግብረሰዶማዊ ሕግ ከናዚ እና ከአፓርታይድ ድርጊት ጋር ማነፃፀራቸውም እየተዘገበ ነው።
የኡጋንዳው የፀረ-ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሕግ በድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎችን ዕድሜ ልክ ከመቅጣት ባሻገር ሁኔታውን እያወቁ በዝምታ የሚያልፉትን ጭምር በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው።
ሕጉ በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ማድረግንም ሆነ በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ መፈፀም፣ ማበረታታትና እያወቁ ዝም ማለትን እንዲሁም በጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ ከሆነም 14 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ያስቀጣል። ሕጉ ከወጣም በኋላ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሕጉ ኋላ ቀር መሆኑን በመጥቀስ አምርረው ተቃውመውታል። በቀጣይ ኡጋንዳ ከአሜሪካ የምታገኘው 400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጥያቄ ምልክት ውስጥ መውደቁ እየተነገረ ነው። ኡጋንዳ የፀረ-ተመሳሳይ ጾታ ሕግ ብታወጣም በሀገሪቱ ድርጊቱ ከተስፋፋባቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል።
ጉዳዩን በተመለከተ የሴቶች የህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ለሰንደቅ እንደተናገሩት ያልታወቁ ሰዎች የሚኒስትር ዘነቡን የቲውተር ገፅ የሚስጥር ቁልፋቸው (Passwords) በመስበር መረጃው መልቀቃቸው አስታውቋል።
የሚኒስትር መስሪያቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብይ ኤፍሬም መረጃው የተሰራጨው የሚኒስትሯ የተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮችንና ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በግላቸው በሚያሰራጩበት የቲውተር ገፃቸው የተለጠፈውን መረጃ ለማጣራት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ጥረት ሲያደርግ መዋሉን ተናግረዋል።
በመጨረሻም በሚኒስትሯ ስም የተሰራጨው መረጃ የሚኒስትሯንም ሆነ የመንግስትን አቋም የማይወክል፣ መሆኑን የቲውተር ገፁም ለጊዜው መታገዱን አመልክቷል።
Source: Sendek

No comments:

Post a Comment