Wednesday, February 19, 2014

ሦስተኛው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

-አብዛኛውን የሹመታቸውን ጊዜ ያሳለፉት በሕመም ነበር
በጳጉሜን 2002 ዓ.ም. መጨረሻ በአዳማ ከተማ በተደረገው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ስድስተኛ ድርጀታዊ ጉባዔ ላይ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠው
ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ በሕመም ምክንያት ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡ ሥልጣናቸውን እስከለቀቁ ድረስ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነት በተጨማሪ የኦሕዴድ ሊቀመንበር ነበሩ፡፡  
አቶ አለማየሁ ከተሾሙ አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላቸው ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መልቀቂያ ቢያቀርቡም፣ የሚተካቸው ሰው ባለመገኘቱ ከሦስት ዓመታት በላይ በኃላፊነት ቆይተው የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቀባይነት በማግኘታቸው ተሰናብተዋል፡፡ 
ፕሬዚዳንቱ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የፈለጉበት ዋናው ምክንያት፣ ሥልጣናቸውን በመስከረም ወር 2003 ዓ.ም. ከቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ ተረክበው ሥራ እንደጀመሩ፣ በምግብ መመረዝ ምክንያት ለሕመም በመዳረጋቸውና አብዛኛውን የሹመታቸውን ጊዜ ያለሥራ በማሳለፋቸው ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ አቶ ዓለማየሁ ለክልሉ ያበረከቱትና ወደፊትም የሚያበረክቱት አስተዋጽኣ ከፍተኛ መሆኑ ቢታመንበትም፣ ያጋጠማቸው ሕመም አሳማኝ በመሆኑ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ማግኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 
ለኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በድጋሚ ያቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ማመልከቻ ተገቢና ትክክለኛ ሆኖ በመገኘቱ ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀርቦለት እንደተቀበለው ተገልጿል፡፡ 
አቶ አለማየሁ በታይላንድና በተለያዩ አገሮች በተደረገላቸው ሕክምና የተሻለ ለውጥ ያገኙ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ እንደፍላጐታቸውና ችሎታቸው መሥራት ባለመቻላቸው፣ ከተረከቡት ከፍተኛ ኃላፊነት ራሳቸውን ማግለል እንደፈለጉ አንዳንድ የቅርብ ጓደኞቻቸው አስረድተዋል፡፡ 
በጳጉሜን 2002 ዓ.ም. የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰይመው በመስከረም ወር 2003 ዓ.ም. ከአቶ አባዱላ ገመዳ ሥልጣኑን የተረከቡት አቶ አለማየሁ፣ የመጀመርያ ትኩረታቸው በክልሉ በስፋት እንደተንሰራፋ እየተነገረ በነበረው የሙስና እንቅስቃሴ፣ በተለይም በመሬት ላይ ተፈጽሟል በተባለው ሙስና እንደነበር የገለጹት የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ አካሄዳቸው በአንዳንድ ኃላፊዎችና ግለሰቦች እንዳልተወደደላቸው አውስተዋል፡፡ 
በአዳማ፣ በሰበታ፣ በቡራዩና በገላን ከተሞች ላይ በመሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ይሠሩ የነበሩ ኃላፊዎች ጭምር በሙስና ተጠርጥረው ከመታሰር እስከ ቅጣት ያለው ሒደት የተፈጸመው በአቶ አለማየሁ ቆራጥ አመራር እንደነበር የሚገልጹት የቅርብ ወዳጆቻቸው፣ የወራት ዕድሜም ሳይቆዩ በምግብ መመረዝ ምክንያት ለሕመም በመዳረጋቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ ምክትላቸው አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ የክልሉን የሥራ እንቅስቃሴ ሲመሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ 
አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እየሠሩ በነበሩበት ወቅት በ2002 ዓ.ም. ምርጫ፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በስሬ ወረዳ ተወዳድረው ለክልሉ ምክር ቤት አባል ሆነው ከተመረጡ በኋላ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል፡፡ አቶ አለማየሁ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች መሥራታቸው ይታወሳል፡፡ 
ከኃላፊነት የመነሳት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ያሰናበታቸው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲሆን አባላቱም አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ፣ አቶ ሙክታር ከድር፣ አቶ ዘለዓለም ጀማነህ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ አቶ ሱፊያን አህመድና አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ናቸው፡፡ በአቶ አለማየሁ ምትክ በቅርቡ ፕሬዚዳንት ይመረጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  
ከአቶ አለማየሁ በፊት የኦሮሚያ ክልልን አቶ ኩማ ደመቅሳና አቶ አባዱላ ገመዳ በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡
source:http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment