Wednesday, February 19, 2014

ሟቾችን መለየት ያልተቻለበት የተሽከርካሪ አደጋ ደረሰ

የካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ (ናዝሬት) በሚጓዘው ሚኒባስ ውስጥ 12 ሰዎች ተሳፍረዋል፡፡
በዚየን ቀን ማለዳ ለተለያዩ ሥራዎችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ የመጡ ተሳፋሪዎች፣ ከቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ለመገናኘት የ99 ኪሎ ሜትር ርቀት አልገፋ ብሏቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀኑ መምሸቱ ነበር፡፡
ባለቤታቸውን በቀበሩ በ12ኛው ቀን የጓደኛቸው ወንድም መሞቱን ሰምተው ለቀብር ወደ አዲስ አበባ የመጡት ወ/ሮ ርግበ መብራህቱም ከተሳፋሪዎቹ አንዷ ናቸው፡፡ በሐዘን የተጐዱ ልጆቻቸውንና የሐዘናቸው ተካፋይ የሆኑ ዘመዶቻቸውን ለመቀላቀል እሳቸውም ልባቸው ተሰቅሏል፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ካለፈ በኋላ አዲስ አበባን ለቆ ወደ አዳማ ያመራው ሚኒባስ፣ የመጨረሻ ፍጥነቱን ተጠቅሞ መብረሩን ተያይዞታል፡፡ እንኳን ምሽትን ተገን አድርጐ ቀርቶ ቀንም ቢሆን ‹‹ኧረ ቀስ በሉ›› ቢባሉ ከማይሰሙ አሽከርካሪዎች አንዱ የሆነው የሚኒባሱ ሾፌር፣ የሚኒባሱን ሙዚቃ ከፍ አድርጐ በመልቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት ይነዳል፡፡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በማለፍ ገላን፣ ዱከም፣ ቢሾፍቱንና ሞጆን ያለፈው ሚኒባስ መጨረሻ ግን አዳማ አልደረሰም፡፡ ሞጆን እንዳለፈ አንድ መጠምዘዢያ ኩርባ ላይ ሲደርስ፣ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ መስመሩን ይዞ ከሚመጣ ኤንትሬ ተሳቧ ጋር ተገናኘ፡፡
ሚኒባሱ ይሄድበት የነበረውን ፍጥነት ቀንሶ ወይም አቁሞ ለማሳለፍ እንደማይችል ያወቀው አሽከርካሪ፣ ደርቦ ማለፍ የመጨረሻው አማራጭ መሆኑን ተረዳ፡፡ በመሆኑም ፍጥነቱን ሳይቀንስ ደርቦ ለማለፍ ሲሞክር የተሳቢው ስፖንዳ ሲመታው ሙሉ በሙሉ በተሳቢው ውስጥ ተቀረቀረ፡፡ ሚኒባሱ አሳፍሯቸው ከነበሩት 12 ተሳፋሪዎች መካከል አንድ ዕድለኛ ተሳፋሪ ከጋቢና ተስፈንጥሮ በመውደቁ ትንሽ ጉዳት ደርሶበት ሲተርፍ፣ ሌሎች ሁለት ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሳባቸው ተረፉ፡፡ አሽከርካሪውን ጨምሮ ስምንት ተሳፋሪዎች ተጨፈላልቀው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በባላቸው ሐዘን ውስጥ የከረሙት ወ/ሮ ርግበ ብቻ አካላቸው ሳይቆራረጥ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይቶ ሲገኙ፣ የቀሪዎቹን ሰባት ማንነት መለየት ባለመቻሉ የአዳማ ማዘጋጃ ቤት ሊቀበራቸው ተገዷል፡፡ በምሥሉ ላይ አደጋውን ያደረሰው ሚኒባስ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ሲታይ፣ ሟች ወ/ሮ ርግበ መብራህቱ እኚህ ነበሩ፡፡ (በታምሩ ጽጌ)

No comments:

Post a Comment