Tuesday, February 25, 2014

በአባይ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር እየተነጋገርኩ ነው አለች

ዋሽንግተን ዲሲ፤ የካቲት 18/2006 (ቢቢኤን) ፦ አራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለዉ ግድብን እንገነባለን በማለት የኢትዮጵያ መንግስት በቦንድ ስም ገንዘብ ለመሰብሰብ ያደረገዉ ሙከራ እምብዛም አለመሳካቱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መንግስት የግንባታዉ ፕሮጀክት ሰላሳ አራት ከመቶ ተጠናቋል ቢልም ግብጽ ባሰማችዉ ተቃዉሞ የግድቡ ግንባታ መስተጓጎሉን የመገናኛ ብዙሗን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ ዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሆኑት አቶ አለማየሁ ተገኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቅረፍ ከሱዳን ጋር ዉይይት ጀምራለች” ሲሉ ገለጸዋል። ግብጽን ወደ ዉይይቱ ሒደት ለማምጣት እየተጣረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ሒደቱ ምን እንደሚመስል ግን ያመላከቱት ነገር የለም።
ሱዳንና ግብጽ ከግድቡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ኢትዮጵያ ብትገልጽም፤ ሁለቱ አገራት ግን ለጉዳዩ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ አልተስተዋልም። ግብጽ ሰማኒያ ከመቶ የሚሆነዉ የዉሃ ሐብቷ ከአባይ እንደሚመጣ ይታወቃል፤ የአባይን ጉዳይ እንደ ህልዉና ስለምትመለከትዉ የህዝብ ድጋፍ የሌለዉ የመላኒየሙ ግድብ እንደምን ዉጤታማ ይሆናል የሚለዉ ጉዳይም አጠያያቂ እየሆነ ነዉ።

ግድቡን ለመገንባት እስከ ሐያ ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያዉያን መፈናቀላቸው የታወቀ ሲሆን 70 ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር ዉሃን ያከማቻል ተብሎ የተነገረት ግድብ ከፈነዳ ከፍተኛ የዉሃ መጥለቅለቅ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ኢትዮጵያ ግድቡ በአዉሮፒያኑ ቀመር 2017 ሲጠናቀቅ እስከ ስድስት ሺ ሜጋ ዋት የሚደርስ የኤለክትሪክ ሐይልን ለማመንጨት ብቃት ይኖረዋል ትላለች። ይህ ዉጥን ከግድቡ ባላንጣዎች ከሱዳናን ግብጽ ብቻ ሳይሆን” አባይ ከመገደቡ በፊት የመብት ጥሰቱ ይከበር” ከሚሉ ኢትዮጵያዉያንም ጭምር ጽኑ ተቃዉሞ እየገጠመዉ ነዉ። ኢትዮጵያ ከፕሮጀክቱ ዋነኛ ባላንጣ ከግብጽ ጋር በቀጥታ መነጋገር ሲገባት፤ ከሱዳን ጋር ዉይይት መጀመሯ ለምን እንደሆነ የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴሩ ግልጽ አላደረጉም።
በተያያዘ ዜናም ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ቀደም ሲል በህዳር 24/2006 ወደ ሱዳን ተጉዘዉ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸዉንና ህወሃት የተመሰረተበትን 39ኛ አመት ለማክበር የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኡመር ሐስን አልበሽር በየካቲት 11/2006 ወደ መቐሌ መጓዛቸዉን ይታወቃል።ይህ ከወትሮ የተለየ ቁርኝት እንደምን ተከሰተ በማለት ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችም አሉ።
የሱዳን የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ አልቀርዲ በህዳር 23/2006 ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸዉን የድንበር ልዩነት አስወግደዉ መስማማታቸዉን ይፋ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ድንበሯን ለሱዳን ቆርሳ ለመስጠት መስማማቷ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያለዉ ብቻ ሳይሆን ህወሃት በስልጣን ለመቆየት የተቃዋሚ ሐይላትን ለመግታት አጎራብች አገራትን እየደለለ ነዉ የሚሉም አሉ።ህወሃት ስልጣኑ በህዝብ ከተወሰደ ሐብትን ወደ አጎራባች አገሮች አሽሽቶ ለመደላደል የሚያደርገዉ ሴራ ይኖራል በማለት ጉዳዩን ከመልካዓምድራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር የሚያይዙም አሉ።
አንድንድ ተንታኞች ደግሞ አባይን መገደብ የሚለዉ ሐሳብ ሶስት ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ አገራት አንባገነናዊ መንግስቶች በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርጉት ወከባ ነዉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በግድቡ ስም ገንዘብ ሲሰበስብ፤ ሱዳንና ግብጽ ደግሞ ብሔራዊ የሆነ ስጋት እንዳንዣበበ በመስበክ ህዝብን የሚያደናግሩበት ትርኢት ነዉ ይላሉ።
ቀድም ሲል ባሶንዳ በሚባለዉ የሱዳን የጠረፍ ከተማና አካባቢ 77 ኢትዮጵያዉያን በሱዳናዉያን መገደላቸዉን ቢቢኤን ዘግቦ ነበር ።ይህ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ ባይታወቅም፤ የሚታወቀዉ ነገር ግን የኢትዮጵያ ዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሆኑት አቶ አለማየሁ ተገኑ የአባይ ግድብ አስመልክቶ ከሱዳን ጋር ዉይይት መኖሩን መናገራቸዉ ነዉ።
በሱዳን ስለሞቱት 77 ኢትዮጵያዉያን የሚናገር ይኖር ይሆን?የኢትዮጵያ እና የሱዳን መንግስታት ስል ድንበር ስምምነት፣የጋራ ስለሆነ ደህነነትና ጥበቃ፣ህገወጥ የሆነ የሰዎች ዝውዉርን ስለመግታት፣የኤለክትሪክ ሐይልን ስለመጋራት፣የአባይን ግድብን አስመልክቶ ስለሚደረጉ ዉይይቶች ብቻ ነዉ እየገለጹ ያሉት።

No comments:

Post a Comment