Saturday, February 22, 2014

ዝምተኛው የአውሮፕላን ጠላፊ

ዝምተኛው የአውሮፕላን ጠላፊ

ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኞች ቀንን በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባከበረበት ወቅት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአየር መንገዱ ደንበኞች አየር መንገዱ ስለደረሰበት የዕድገት ደረጃ ዝርዝር ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር፡፡
የአገር ባህል ልብስ ለብሰው ፈገግታ ሳይለያቸው የአየር መንገዱን ስኬት ሲያስረዱ ‹‹ዋካ ዋካ›› በሚለው በሻኪራ ተወዳጅ ዜማ ታጅበው ነበር፡፡ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት አብዱሰላም አቡበከር፣ ታዋቂ ባለሀብቶችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በዚህ ደማቅ ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ተወልደ የአየር መንገዱን ስኬት በኩራት አስረድተዋል፡፡

በእርግጥም አየር መንገዱ ባለፉት አምስት ዓመታት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ቁጥር 79 አድርሷል፡፡ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ደግሞ ወደ 63 አሳድጓል፡፡ እጅግ ዘመናዊ የሚባለውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እጁ በማስገባት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ሦስተኛው አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል፡፡ ገቢውን በሰባት እጥፍ በማሳደግ 2.1 ቢሊዮን ዶላር አድርሷል፡፡
የዚያን ዕለት በአየር መንገዱ ስኬት ሲፍነከነኩ የነበሩትን አቶ ተወልደን ለተመለከታቸው ሰው፣ ከአንድ ቀን በኋላ አስደንጋጭ ዜና ይነገራቸዋል ብሎ በፍፁም ሊያስብ አይችልም ነበር፡፡ የሆነው ግን እንደዚያ ነው፡፡
እሑድ የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ 202 መንገደኞችንና የአውሮፕላኑን ሠራተኞች አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ይጓዝ የነበረው ቦይንግ 767-300 አውሮፕላን፣ ከአንድ ሰዓት በረራ በኋላ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ እንደገባ በረዳት አብራሪው ኃይለመድኅን አበራ ተገኝ ተጠልፎ ወደ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ እንዲጓዝ ተደረገ፡፡ ዋና አብራሪው ጣሊያናዊው ካፒቴን ፓትሪዚዮ ባርቤሪ ወደ መፀዳጃ ቤት ሲሄዱ ጠብቆ የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍሉን በር ከውስጥ ቆልፎ አውሮፕላኑን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው ኃይለመድኅን (ቤተሰቦቹ ታዴ ብለው ነው የሚጠሩት) አውሮፕላኑን በጄኔቭ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም አሳርፎ እጁን ለስዊዘርላንድ ፖሊስ ሰጥቷል፡፡
ኃይለመድኅን በአገሩ የመኖር ዋስትና እንዳጣ በመግለጽ የስዊዘርላንድ መንግሥት ጥገኝነት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፖሊስ በኃይለመድኅን ላይ ምርመራ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ የስዊዘርላንድ መንግሥት ጠበቃ አቁሞለታል፡፡ ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁሌም የአውሮፕላን ጠለፋ በውጭ ሰው የሚከናወን በመሆኑ የኃይለመድኅን የበረራ ቁጥር ‹‹ET 702›› በረዳት አብራሪው መጠለፉ አስገራሚ አድርጐታል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ በመላው ዓለም የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ድርጊቱ የጤና ነው ወይ የሚል ጥያቄም አስነስቷል፡፡ በረዳት አብራሪው የአዕምሮ ጤንነት ላይ ጥያቄ መሰንዘር ተጀምሯል፡፡
የኃይለመድኅን ታናሽ እህት ትንሳኤ አበራ በፌስቡክ ገጿ ላይ ባስነበበችው ጽሑፍ ወንድሟ መጠነኛ የሆነ የአዕምሮ መታወክ ገጥሞት እንደነበር ይፋ አድርጋለች፡፡ ከቤተሰብና ጓደኞቹ ራሱን ማግለል፣ ሊያጠቁት የፈለጉ ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች እንደሚከታተሉት በማሰብ በሥጋት መኖር፣ ወንድሟ ካሳያቸው የተለዩ ባህሪያት መካከል ይገኙበታል፡፡ ኃይለመድኅን እርሱ በሌለበት ቤቱ እንደሚበረበር በማሰብ በቤቱ ውስጥ የቅኝት ካሜራ እስከመስቀል እንደደረሰ ትንሳኤ ተርካለች፡፡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምምልስ ያደረጉት ታላቅ ወንድማቸው ዶ/ር እንዳላማው አበራ ወንድማቸው የአዕምሮ ጤንነት ችግር ገጥሞታል ብለው እንደሚጠረጥሩና እህቶቹ ኃይለመድኅን የሥነ አዕምሮ ሐኪም ዘንድ እንዲሄድ እንደመከሩት ተናግረዋል፡፡
የኃይለመድኅን ጐረቤቶች በበኩላቸው ዘወትር ብቻውን የሚታይ፣ ዝምተኛና ሰላምተኛ ሰው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ኃይለመድኅን የሚኖረው ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ሳሚ ሕንፃ ጀርባ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ብሎክ ሰባት በመጀመሪያ ፎቅ ከሚገኝ ባለ አንድ መኝታ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ጠለፋው ከተፈጸመ በኋላ ቤቱ በፖሊስ የተፈተሸ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ በፌዴራል ፖሊስ አባላት የሚጠበቅ በመሆኑ ማንም ወደ ቤቱ ውስጥ መግባት አይፈቀድለትም፡፡ ከመርማሪ ፖሊሶች በስተቀር፡፡
የኮንዶሚኒየሙ አንድ የጥበቃ አባል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኃይለመድኅን በግቢው ውስጥ ለአምስት ዓመታት ተከራይቶ ኖሯል፡፡ ኃይለመድኅን ወደ ቤቱ ሲገባና ሲወጣ ከሰው ጋር አይታይም፡፡ ጓደኛም ይዞ አይመጣም፡፡ ‹‹ሲገባና ሲወጣ ሰላምታ ይሰጠናል፡፡ ከዚያ ውጪ ከሰው ጋር ክፉም ሆነ ደግ ሲነጋገር አይተነው አናውቅም፤›› ያሉት የጥበቃ አባል፣ ኃይለመድኅንን መጨረሻ ያዩት እሑድ የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹እንደተለመደው ቲሸርትና ቁምጣውን አድርጐ በግቢው ደጃፍ ከሚገኘው አነስተኛ የገበያ አዳራሽ (Mini Market) ዕቃ ገዝቶ የተለመደውን ሰላምታ ሰጥቶን አልፏል፡፡ ከዚያ በኋላ አላየሁትም፤›› ያሉት ጥበቃው በወቅቱ የተለየ ነገር እንዳላዩበት ተናግረዋል፡፡
በሳሚ ሕንፃ ወደ ውስጥ በተነጠፈው ኮብልስቶን መንገድ በስተግራ በኩል ባለው የኮንዶሚኒየም ግቢ ደጃፍ ምግብ ቤት፣ ኢንተርኔት ቤት፣ ግሮሰሪና አነስተኛ የገበያ አዳራሽ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ንግድ ቤቶች አንዱ በሆነው ተክሌ ግሮሰሪ ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራው ወጣት መቅደስ፣ ኃይለመድኅንን ለአራት ዓመት ያህል ታውቀዋለች፡፡ ‹‹ስሙ ኃይለመድኅን መሆኑን ያወቅነው ከሚዲያ ነው እንጂ እኛ ታዴ በሚል ስም ነው የምናውቀው፤›› ያለችው መቅደስ፣ ኃይለመድኅን ብዙ ጊዜ ቁርስ ለመመገብ ወደ ተክሌ ግሮሰሪ እንደሚመጣ ተናግራለች፡፡ እንቁላል ፍርፍር ወይም እንቁላላ በሥጋ አዘውትሮ ለቁርስ እንደሚመርጥ የምትናገረው መቅደስ፣ ኃይለመድኅን ዝምተኛና ብቸኛ ሰው እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
ወደ ግሮሰሪው የሚመጣው ብቻውን እንደሆነና መጠጥ ሲጠጣ አይታው እንደማታውቅ ገልጻለች፡፡ ‹‹በጣም ሰላማዊ ሰው ነው፡፡ ምን ዓይነት ነገር እዚህ ውስጥ እንደከተተው እግዚአብሔር ይወቅ፤›› ብላ፣ ዓርብ ዕለት የወሰደውን የአንድ ጠርሙስ ጉደርና እሑድ ዕለት የወሰደውን ሁለት ጠርሙስ ማልታ (አልኮል የሌለው የሜታ ምርት) ሒሳብ እሑድ ከሰዓት በኋላ ሰጥቷት እንደሄደ በትካዜ ታስታውሳለች፡፡
በተክሌ ግሮሰሪ በአስተናጋጅነት ለሦስት ዓመት ያህል የሠራው ጐሳዬ የተባለው ወጣት፣ የኃይለመድኅን ሽርክ እንደሆነ በሠፈሩ ይነገራል፡፡ ጐሳዬ ኃይለመድኅንን የሚያውቀው በተክሌ ግሮሰሪ ተቀጥሮ ሲሠራ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ኃይለመድኅን ዕረፍት በሆነባቸው ቀናት በስልክ የሚፈልገውን ምግብ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ የሞባይል ካርድ የመሳሰሉትን እንዲያመጣለት እንደሚያዘውና የጠየቀውን በፍጥነት እንደሚወስድለት ተናግሯል፡፡
‹‹ፀባዩ ይመቸኛል፡፡ በጣም ዝምተኛ ነው፡፡ ሲበዛ ጥሩ ሰው ነው፡፡ ከአፉ ክፉ ነገር አይወጣም፡፡ ከስንቱ ጋር በሒሳብ ስጨቃጨቅ እርሱ ግን አንድም ቀን ተከራክሮኝ አያውቅም፡፡ ያዘዘኝን እወስድለታለሁ ሒሳቡን አስቦ ከነጉርሻው ይሰጠኛል፡፡ አጋጣሚ ሳይከፍለኝ ወደ ሥራ ከሄደ ከበረራ ሲመለስ ራሱ ደውሎ ናና ሒሳብህን ውሰድ ይለኛል፤›› ያለው ጐሳዬ፣ ኃይለመድኅን ቤት ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅ፣ የጠየቀውን ዕቃና ገንዘብ የሚለዋወጡት ቤቱ በር ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ኃይለመድኅንን ባገለገለገባቸው ሦስት ዓመታት አንድም ጊዜ ከሰው ጋር አይቶት እንደማያውቅ ጐሳዬ አስረድቷል፡፡
‹‹ዕረፍት ከሆነ ከቤቱ አይወጣም፡፡ ያዘዘኝን ላደርስ ቤቱ ስሄድ ፊልም ሲመለከት ነው የማገኘው፡፡ እቤቱ ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ አይቼ አላውቅም፤›› ብሏል፡፡ ኃይለመድኅንን በፀባዩ በጣም እንደሚወደውና በገጠመው ነገር በጣም ማዘኑን የሚናገረው ጐሳዬ፣ በቅርቡ ነጭ መኪና መግዛቱን ተናግሯል፡፡
የኃይለመድኅን ጐረቤቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሰላምታ ያለፈ ከእነርሱ ጋር ቅርርብ የለውም፡፡ ይልቁንም ኃይለመድኅን በዕረፍቱ ቀናት (በረራ ሳይኖረው) ረዥም ጊዜ የሚያሳልፈው መሲ ቢዝነስ ሴንተር በተባለው ቤት ኢንተርኔት በመጠቀም እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
መሲ ቢዝነስ ሴንተር የሚገኘው በኮንዶሚኒየሙ ግቢ በውጪ በኩል ጥግ ላይ ነው፡፡ የቢዝነስ ሴንተሩ ባለቤት ወ/ሮ መሠረት ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡ መሠረት ኢንተርኔት ቤቱን ከከፈተች ሰባት ወር እንደሆናት፣ በዚህም ጊዜ ኃይለመድኅን ዋና ደንበኛዋ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ ‹‹ዕረፍት ከሆነ እኛ ጋር ይመጣል፡፡ ለረዥም ሰዓት ይቀመጣል፡፡ በኢንተርኔት የሚከታተለው የውጭ ፊልም አለ፡፡ አስቂኝ ፊልም ሳይሆን አይቀርም ፊልሙን እያየ ይስቃል፤›› ብላለች መሠረት፡፡
‹‹የሚመለከተው ነገር ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያለው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የሚቀመጥበት ቦታ ማንም ሰው ከኋላው ወይም በረንዳው ላይ እንኳ ሆኖ ሊመለከተው ይችላል፤›› የምትለው መሠረት፣ ኃይለመድኅን ዝምተኛና መልካም ፀባይ ያለው ሰው እንደሆነ ትመሰክራለች፡፡
ሳሚ ሕንፃ ፊት ለፊት ጫማ ከሚጠርጉት ሊስትሮዎች መካከል አንዱ የሆነው አሸናፊ በቀለ ኃይለመድኅን ደንበኛው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የ15 ዓመት ታዳጊ የሆነው አሸናፊ የኃይለመድኅን ጫማን ቀለም በቀባ ቁጥር ስድስት እስከ አሥር ብር እንደሚሰጠው ይናገራል፡፡ ክሬም ጫማ ለመቀባት የሚያስከፍለው ስድስት ብር ቢሆንም ኃይለመድኅን አሥር ብር እንደሚሰጠው በፈገግታ ያስታውሳል፡፡
የአካባቢው ሰዎች ኃይለመድኅንን የሚገልጹት በተመሳሳይ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ ዝምተኛ፣ ብቸኛና ሰላማዊ ሰው ነው በማለት፡፡ ኃይለመድኅን የአዕምሮ ጤንነቱ እንደታወከ በሥነ አዕምሮ ሐኪሞች ማረጋገጥ ከተቻለ ከፍርድ ነፃ ሊወጣ እንደሚችል ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉ ድርጊቶችን በትክክል በአዕምሮ ጤና መታወክ የተፈጸሙ መሆኑን ፍርድ ቤትን ማሳመን የሕግ ባለሙያዎችን የሚፈትን ከባድ ሥራ እንደሆነ የሕግ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በአውሮፕላን ጠለፋው ዙሪያ ባለፈው ማክሰኞ ከሰጡት መግለጫ ውጪ የምጨምረው የለም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝምታን መርጧል፡፡
አቶ ሬድዋን የረዳት አብራሪውን የአዕምሮ ጤንነት በተመለከተ ተጠይቀው አየር መንገዱ እስከሚያውቀው ድረስ ግለሰቡ ጤነኛ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አብራሪዎች በየጊዜው ሙሉ የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ገልጸው፣ የምሥለ በረራ ሥልጠና በሚወስዱ ጊዜ ጭንቀትን (Stress) የመቋቋም ብቃታቸው ይታያል ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ የምናውቀው አቶ ኃይለመድኅን ብቁ (Qualified) አብራሪ መሆኑን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ባለበት ወቅት በተፈጠረ አንድ ክስተት ምክንያት የገነባው መልካም ስምና ዝና ሊናድ አይገባም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 8,000 ሠራተኞች ሲኖሩት፣ 651 አብራሪዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል 100 ያህሉ የውጭ ዜጐች ናቸው፡፡ ‹‹ስምንት ሺሕ ሠራተኞች ባሉበት ኩባንያ ውስጥ አንድ ሰው ባደረገው ድርጊት ሁሉም ነገር በዜሮ ሊባዛ አይችልም፣ አይሆንምም፤›› ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment