Monday, February 24, 2014

ዩክሬይን የጂኦፖለቲካ ሽኩቻ ምድር

በሁለት ሺሕ አራት በተደረገዉ የአደባባይ ሠልፍ ለስልጣን የበቁት የብርቱካናማዉ አብዮት መሪዎች ቪክቶር ዮሼቼንኮ እና ወይዘሮ ቲሞሼንኮ ሥልጣን በያዙ ማግስት ተጣልተዉ ሥልጣናቸዉንም፥ የሕዝቡንም ጉጉት፥ የምዕራቦችንም ተስፋ መና አስቀርተዉታል።ወደፊትም ያለፈዉ ላለመደገሙ ምንም ዋስትና የለም።
በሕዝባዊ አመፅ፣ ተቃዉሞ? ግጭት መሪዎችን በመሻር-መሾም የተካነችዉ ሐገር ዘንድሮም ደም ባራጨ አመፅ ግጭት መሪዋን ዳግም ሻረች።ዩክሬን። የየዘመኑን ተቀናቃኝ ሐያል ተፅዕኖ፥ ሽኩቻ ያላስተናገደችበት ዘመን የለም።ዘንድሮም ደገመችዉ።የዋሽግተን-ብራስልስ ሐያላን ደጋፊ-አድናቂዎች ኪየቭ ላይ ዳግም ድል አደረጉ።የሞስኮ ተከታይ ተቀናቃኞቻቸዉ ኮበለሉ።ሥልታዊ ናት፥ ሐብታም፥ የዕሕል ጎተራ።በቅጡ ተመርታ፥ በነፃነት ተረጋጋታ ኖራ ግን አታዉቅም።ዩክሬን።የቅዳሜዉ ድል-ሽንፈት መነሻ፥ያለፈ ተመሳሳይ ታሪኳ መጣቀሻ፣ ምክንያት መልዕክቱ መድረሻችን ነዉ፣-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሰዉ ከአርባ ሺሕ ዘመን በላይ ኖሮባታል።ፈረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገርቶ-ወደ ቤት እንሰሳነት ተለዉጦባታል።ዩክሬን።ቫራንጊነሶች በዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን የመሠረቱት የምሥራቅ ሥላቮች አገዛዝ ሩስ-ወይም ሩሲያ (በላቲኖቹ) በመካከለኛዉ ክፍለ-ዘመን ከአዉሮጳ ጠንካራ ንጉሳዊ ሥርወ-መንግሥት አንዱ ነበር።
ብዙዎቹ ነገስታት ግን አንድም የአጎራባች ጠንካሮች፥ ዓለያም የዓለም ሐያላን ድጋፍ ወይም ዝርያ የነበራቸዉ እንጂ የራስዋ አንጡራ ተወላጆች አልነበሩም።እንደ ሐገር የምትታወቅበት ግዛትም በየዘመኑ እንደየገዢዋችዋ ጥንካሬ ሲሰፋ ሲጠብ ነዉ የኖረዉ።በጥናት በርግጥ አልተረጋገጠም ምናልባት እንደፈረስ ሁሉ ሕዝባዊ አመፅንም ለዓለም ሳታስተዋወቅ አልቀረም።ይሕ ቢቀር ለራስዋ ሕዝባዊ አመፅ የተጀመረባት በ1653 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነበር።
በ1569 የፖላንድ ነገስታት ይገዟት ገቡ።መቶ ዓመት ግን አልዘለቁም።በ1653 አብዛኛዉ የዩክሬን ሕዝብ ሐገሩን የሚገዙትን የፖላንድ ካቶሊኮች በመቃወም አመፀ።ከወራት አመፅ ተቃዉሞ በኋላ ፖላንዶች ጓዛቸዉን ጠቅልለዉ ሲወጡ ሩሲያዎች ያቺን ሐገር ተቆጣጠሯት።1654።


የዉጪ ሐያላን ሽኩቻ፥ ግጭትና ጦርነት፥ ሕዝባዊ አመፅ፥ የርስ በርስ ትርምስ የገራት ያቺ ምሥራቅ አዉሮጳዊያት ሐገር ዛሬም፥ ጀርመናዊዉ የፖለቲካ አዋቂ አሌክሳንደር ራሕር እንደሚሉት የሰወስት ወገኖች ጥቅም እሰወስት ያተረምሳታል።

«ዩክሬን ዉስጥ ሰዎስት ግንባሮች አሉ።የመጀመሪያዉ ግንባር አደባባይ ከወጣዉ ሕዝብ አብዛኛዉን የያዘዉ ነዉ።ይሕ ግንባር የሚያስተናብራቸዉ ወገኖች ሙስናን የሚቃወሙ፥ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚጠይቁ ናቸዉ።ሁለተኛዉ ግንባር በዩክሬይን ምዕራብ እና ምሥራቅ ግዛት የሚከፈል ነዉ።የምዕራቡ ግንባር የኬየቭ አካባቢ ነዋሪዎችን የሚይዘዉ (ፕሬዝዳት) ያኑኮቪችን የሚቃወሙት ናቸዉ።የምሥራቁ ግንባር ባንፃሩ የምዕራብ ዩክሬን ተወላጅ በሚመራዉ መንግሥት አንገዛም ወይም አንመራም የሚለዉ ሐይል ነዉ።ሐገሪቱ ከአሥራ-አምስት ዓመት በፊት በዩጎዝላቪያ ሰርቦችና ክሮኤሽዎች መካካል የነበረዉ አይነት ሁኔታ የተከፈለች ናት።»

የመጀመሪያዉ ግንባር የሚያስተናብረዉ ሕዝብ ቁጥሩ ብዙ፥ ጥያቄዉም ፍትዊ፥ ነዉ።አብዛኞቹ ፖለቲከኞች የዚያን ሕዝብ ፍትሐዊ ጥያቄ የሚያቀነቅኑት የኪየቭን ቤተ-መንግሥት እስኪረከቡ፥ የምዕራብ ምሥራቅ ደጋፊዎቻቸዉን ፍላጎት እስኪያሟሉ ድረስ መሆኑ ነዉ-ቁጭቱ።ክፍፍሉ የፖለቲካ ተንታኙ እንዳሉት ከሕዝብ የአስተሳሰብ ልዩነት አልፎ የግዛት ሽንሸና ከሚያስከትልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም።መከፋፈል ግን ለዚያች ሐገር እንግዳ አይደለም።

ከ1772 እስከ 1795 በነበሩት ዓመታት የዛሬዋ ፖላንድን ለሁለት ሥትገመሥ የያኔዎቹ ሐያላን ሩሲያና ኦስትሪያ ዩክሬንንም ለሁለት ተቃርጠዉ ይገዟት ያዙ።የሩሲያ አብዮት ለዩክሬን የአንድነት ተስፋ፥ የነፃነት ብሥራት ይዞ ነበር ብቅ ያለዉ።ወዲያዉ ግን ዩክሬኖች ከርስ በርስ ጦርነት ተዘፈቁ።የጦርነቱ ፍፃሜ የዩክሬን ሕዝባዊት ሪፐብሊክ የተሰኘችዉን ነፃ ሐገር አስከተለ።1919 ።ወዲያዉ ግን ሌላ ጦርነት።የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት።
ጦርነቱ በሩሲያ ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ ዩክሬንም የሶቪየት ሕብረት ሶሻሊስት ሪፐብሊኮች አባል ሆነች።ኮሚንስት።የፖለቲካ ተንታኝ አሌክሳንደር ራሕር እንደሚሉት ከኮሚንስታዊ ሥርዓት በፊትም የነበረዉ የሩሲያዎች ተፅዕኖ በኮሚንስታዊ ዘመን ተጠናከረ።ተፅኖዉ ፖለቲካዊ፥ ርዕዮተ ዓለማዊ፥ ምጣኔ ሐብታዊ ብቻ አይደለም።
«በተለይ ምሥራቅ ዩክሬን በጣም ሩሲያዊ ሆናለች።እዚያ ሃያ ሚሊዮን ሩሲያዎችም ይኖራሉ።አርባ ሚሊዮን ዩክሬናዊ በየቤቱ ሩሲያኛ ይናገራል።የሩሲያን ባሕል እና የአኗኗር ዘይቤ ይዞ ነዉ ያደገዉ።ይሕ አካባቢ በሶቬት ሕብረት ዘመን የተገነቡ ኢንዱስትሪዎች ያሉበት፥የሶቬየት ሕብረት የዳበረ የብረት ማዕድን የሚገኝበት አካባቢ ነዉ።»
1990።ሌላ አጋጣሚ፥ ሌላ ሠልፍ፥ ሌላ ታሪክ።ነገሩ እንዲሕ ነዉ።የሶቭየት ሕብረት የመጨረሻ ገዢ ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ታላቅ፥ ሐያል ኮሚስታዊት ሐገራቸዉን ለመፈረካካስ ካናቷ ሲወቅሯት ዩክሬኖች አጋጣሚዉን በ1919 ተመስርቶ የነበረዉን አንድነት ለማስታወስ በሚል ሰበብ አደባባይ ወጡ።
ጥር ሃያ-አንድ።ከሰወስት መቶ ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ ከርዕሠ-ከተማ ኪየቭ እስከ ጥንታዊቷ ከተማ ልቪቭ ከተማ ድረስ እጅ ለእጅ ተያይዞ-በሰልፉ ታደመ።ባመቱ ዩክሬን ከሶቬት ሕብረት ተገንጥላ ነፃነቷን አወጀች።ነሐሴ-1991።
የአዲሲቱ ዩክሬን የመጀመሪያ ፕሬዝዳት ሊወኒድ ክራቭቹክ የአዲሲቱ የሩሲያ ፌደሬሽን ፕሬዝዳት ቦርስ የሊሲንንም፥ የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተንንም፥ የብራስልስ መሪዎችንም አማክለዉ እንደያዙ ያቺን ሐገር ይገዙ ገቡ።ክራቭቹክ በ1994ቱ ምርጫ በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትራቸዉ በሊወኒድ ኩችማ ተሸንፈዉ ሥልጣናቸዉን ላሸናፊዉ ሲያስረክቡ ያቺ ሐገር የመጀመሪያዉን ሠላማዊ፥ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር የማድረጓ አብነት ሆኖ ነበር።

ከአስር ዓመት በኋላ ግን የነበረዉ በነበረበት አልቀጠለም።ጎርቫቾቭ ሶቭየት ሕብረትን እንዳደረጉት የሊስንም ሩሲያን ሲሆን ገደለዉ፥ ይሕ ቢቀር በትነዉ ይሔዳሉ ሲባሉ ቭላድሚር ፑቲን ለሚባሉ ሐይለኛ የቀድሞ ሠላይ ወጣት ፖለቲከኛ አስረክበዉ ተሰናበቱ።
የፑቲኗ ሩሲያ በምጣኔ ሐብቱ እየፈረጠመች፥ በጦር-ፖለቲካዉ እየተጠናከረች ባካባቢዉ የምታሳርፈዉ ተፅዕኖ ዳግም ሲያይል ዩክሬንም ዳግም የምዕራብ ምሥራቆች መሻኮቻ ሆነች።በሁለት ሺሕ አራቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተወዳደሩት የፕሬዝዳት ኩችማንና የቪክቶር ዩሼቼንኮ ዉዝግብ የሞስኮ-ብራስልስ-ዋሽግተኖች ፍትጊያ የታየበት ነበር።
በምርጫዉ ለሞስኮ ይወግናሉ የሚባሉት ፕሬዝዳት ኩችማን አሸነፉ መባሉ፥የምዕራቦችን ቀልብ የሳቡትን የዩሼቼንኮ እና የተባበሪያቸዉን የወይዘሮ ዩሊያ ቲሞሼንኮን ቁጣ ሲቀሰቅስ-ዩክሬን ለሌላ ሕዝባዊ ሠልፍና ግጭት ታደመች።ስሙንም ብርቱካናማዉ አብዮት አሉት።ከወራት
ሠልፍ፥ ግጭት፥ ዉዝግብ በኋላ አብዮተኞቹ ድል አድርገዉ ዩሼቼንኮ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን በዳግም ምርጫ ተቆጣጠሩ።ድል ለምዕራቦች።ምስኮዎች ግን አንቀላፉ እንጂ አልተኙም።

ስድስት ዓመት አዝግመዉ በ2010 በተደረገዉ ምርጫ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ያኑኮቪች የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን ያዙ።የያኑኮቪች ድል ለሞስኮዎች ብሥራት ለምዕራቦች መርዶ ብጤ ነበር።ፕሬዝዳት ያኑኮቪች ባለፈዉ ሕዳር ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር የመተባበር ስምምነት አልፈርምም ማለታቸዉ ግን ሰወስት ዓመት ያልፀናዉን የሐይል አሠላለፍ ባዲስ መልክ ለማሾር ዋና ሰበብ ምክንያት ሆነ።

ኪየቭ እንደገና በተቃዉሞ ሠልፍ ተጥለቀለቀች።ዉሎ ሲያድር እንደገና በግጭት፥ ግድያ፥ ድብድብ አደፈች።ከሕዳር አጋማሽ እስካለፈዉ ቅዳሜ በቀጠለዉ ሰልፍ፥ ግጭት፥ በትንሽ ግምት ሰባ ሰዎች ተገድለዋል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።ወትሮም ያላማረበት የዩክሬን ምጣኔ ሐብት ጨርሶ ተሽመድምዷል። አንዳድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ዩክሬንን ከሕዳር በፊት ወደነበረበችበት ለመመለስ እስከ አስራ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።

የተቃዉሞ ሠልፍ ዉዝግቡ ወደ አስከፊ ግጭት መለወጡን የሩሲያም፥ የአዉሮጳ ሕብረትም የዩናይትድ ስቴትስም ፖለቲከኛና ዲፕሎማቶች ተቃዉመዉታል።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይንማየር ከቀዳሚዎቹ አንዱ ነበሩ።

«ለበርካታ ዕለታትና ሳምንታት የተሰለፉት ተቃዋሚዎች ምንም ዓይነት ለዉጥ ባለማየታቸዉ የሚገባቸዉን ሥጋት እገነዘባለሁ።ያም ሆኖ አቋማችን አልተለወጠም።ግጭት ለዩክሬን መፍትሔ አይሆንም።ይሕን የምንናገረዉ ለሁለቱም ወገኖች ነዉ።»

በሩሲያ፥ በጀርመን፥ በፈረንሳይ እና በፖላንድ ግፊት መንግሥትና ተቃዋሚዎች ግጭቱን ለማቆም ተስማምተዉ ባለፈዉ አርብ ተፈራርመዉ ነበር።ይሁንና ያ የዓለም የቦክሰኞች ቦክሰኛ ቪታሊ ክሊትችኮ (ፖለቲከኛ ሲሆን አንቱ ነዉ) እንደ ቦክስ ተጋጣሚዎቹ ሁሉ የዩኑኮቪችን መንግሥት መንጋጋ ሳይመነግል ማረፉን አልፈቀደም።

በርግጥም ሕዳር የጀመረዉን ቅዳሜ ፈጠመዉ።ዩኑኮቪች ቤተ-መንግሥታቸዉን ጥለዉ ፈረጠጡ።ግን ደግሞ እንዲሕ አሉ።

«በጣም ርግጠኛ ነኝ ይሕ አሁን ሐገራችንም፥ መላዉ ዓለምም የተመለከተዉ የመፈንቅለ መንግሥት ምሳሌ መሆኑ ግልፅ ነዉ።ዩክሬን ትቼ የትም አልሆድም።ሥልጣኔን አለቅምም።በምርጫ ሥልጣን የያዝኩ ሕጋዊ ፕሬዝዳት ነኝ።አብሬያቸዉ ከሠራኋቸዉ ዓለም አቀፍ ሸምጋዮች በሙሉ ደሕንነቴ እንደሚጠበቅ ዋስትና ሰጥተዉኛል።ይሕን ሚናቸዉን እንዴት እንደሚያሟሉት እጠብቃለሁ።»

እስከ ዛሬ የት እንዳሉ አይታወቅም።በዘመነ-ሥልጣናቸዉ በማጭበር ወንጀል አስከስሰዉ እስራት ያስበየኑባቸዉ የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚንስትር፥የብርቱካናማዉ አብዮት መሪ ወይዘሮ ዩሊያ ቲሞሼንኮ ባንፃሩ ከሆስፒታል ወጥተዉ ድሉን ተቋደሱ።ዩክሬን ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር መተባበር አባልም መሆን አለባት የሚሉት ሐይላት አሸንፈዋል።ሩሲያዎች ተሸነፉ።


በሁለት ሺሕ አራት በተደረገዉ የአደባባይ ሠልፍ ለስልጣን የበቁት የብርቱካናማዉ አብዮት መሪዎች ቪክቶር ዮሼቼንኮ እና ወይዘሮ ቲሞሼንኮ ሥልጣን በያዙ ማግስት ተጣልተዉ ሥልጣናቸዉንም፥ የሕዝቡንም ጉጉት፥ የምዕራቦችንም ተስፋ መና አስቀርተዉታል።ወደፊትም ያለፈዉ ላለመደገሙ ምንም ዋስትና የለም።

የፖለቲካ ተንታኝ አሌክሳንደር ራሕር እንደሚሉት ደግሞ ድል ሽንፈቱ በዚሕ አይቀጥልም።

«እዚሕ የምናየዉ የበርሊን ግንብ ከፈረሰ ወዲሕ አዉሮጳ ዉስጥ ከፍተኛዉን ግጭት ነዉ።ዩክሬን ዉስጥ የምዕራቦችና የሩሲያ ጥቅም ክፉኛ እየተጋጨ ነዉ።እኔ መስኮቱን ጥላሸት መቀባት አልፈልግም ይሁንና ዩክሬን የአዉሮጳ ሕብረት ወይም የኔቶ አባል ከሆነች፥ ሩሲያን የሚፃረር አንድ አዲስ ግንባር መሠረትን ማለት ነዉ።እና ሩሲያ ከኛ ጋር የቀዝቃዛዉ ጦርነት አይነት ፍትጫ ዉስጥ ትገባለች።ሁለቱም ወገኖች መቀራረብ አለባቸዉ።»

ዩክሬን አርባ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ አላት።የአንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ምጣኔ ሐብት ይዘወርባታል።በቴክኖሎጂ የዳበረች ናት።በሕዝብ ብዛት፥ በምጣኔ ሐብት፥ በቴክኖሎጅም ከቀድሞ የሶቬት ሕብረት ሪፐብሊኮች ከሩሲያ በስተቀር የሚበልጣት የለም።በብረት ማዕድንና በእርሻ የበለፀገች ናት።
ከአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የጋስ ፍጆታ ሃያ-አምስት ከመቶዉ የሚቀዳዉ ከሩሲያ ነዉ።ከጋሱ ሰማንያ በመቶዉ የሚያልፈዉ ደግሞ በዩክሬን በኩል ነዉ።አፄ ቴዎድሮስ አንድ መድፋቸዉን የሰየሙበት ሳቫስቶፖል-የሩሲያ ባሕር ሐይል ትልቅ ጦር ሠፈር ይገኝባታል።ሩሲያ ዩክሬንን ለምዕራቡ አትለቅም።ምዕራቡም ዩክሬንን ለሩሲያ ብቻ አይለቅም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ

No comments:

Post a Comment