Wednesday, February 19, 2014

ሦስት የግብፅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲቋረጥ አቤቱታ አቀረቡ

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ሲካሄድ የቆየው የሦስትዮሽ ውይይት ከተቋረጠ ከሳምንታት በኋላ፣ ሰሞኑን ሦስት የግብፅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

‘ዲሞክራቲክ ፒፕል ፓርቲ’፣ ‘ኢጂፕቲያን ዓረብ ሶሻሊስት ፓርቲ’ እና ‘ሶሻል ጀስቲስ ፓርቲ’ የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ዘ ሄግ ለሚገኘው ዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታቆም የሚጠይቅ ማመልከቻ አስገብተዋል፡፡
ግብፅ በየዓመቱ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ከዓባይ ተፋሰስ እንደምትጠብቅ የተናገሩት የዲሞክራቲክ ፒፕል ፓርቲ ሊቀመንበር ፉአድ ሃፌዝ፣ ባለፈው መስከረም ወር የወንዙ ፍሰት በ20 ቢሊዮን ኪዩቡክ ሜትር ቅናሽ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡
የፍርድ ቤቱን አንቀጽ 40 እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አንቀጽ 96 በመጥቀስ አቤቱታ ማቅረብ መብታቸው መሆኑን የተናገሩት የፓርቲዎቹ መሪዎች፣ ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳትገነባ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በመስኖ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ፍርድ ቤቱ በፓርቲዎች የሚቀርቡ ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን የለውም ብለዋል፡፡
አቶ ፈቅአህመድ እንዳሉት፣ ግብፅ ወደ የትኛውም ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ብትወስደው ኢትዮጵያ የሚያስፈራት ነገር የለም ብለው፣ አቤቱታው የቀረበለት ፍርድ ቤት ጉዳዩን መመልከት የሚችለው በሁለት ሉዓላዊ አገሮች መልካም ፈቃድ የቀረበ እንደሆነ ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐዜም አል ቤብላዊ፣ ‹‹የዓባይ ውኃ የሚወክለው የግብፅን ህልውና ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንን ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ የመጠቀም መብት እንዳላት አምነዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግድብ መገንባት እንደምትችል፣ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በሦስቱ አገሮች መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ውይይት መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት መጀመሩ ሦስቱንም አገሮች ቢጠቅም እንጂ ፈጽሞ አይጐዳም የሚል እምነታቸውን ያንፀባረቁ ቢሆንም፣ የውይይቱ አጀንዳ እንዲሆን የሚፈልጉት ግን ኢትዮጵያ በማትቀበለው የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተሳትፎ ላይ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment