Wednesday, February 19, 2014

እነ አቶ መላኩ ፈንታ ተቃውሞ አቀረቡ

-የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል
በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገብርዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ በከባድ የሙስና ወንጀል
ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ነጋዴዎችና የተለያዩ ግለሰቦች፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ላይ ለፍርድ ቤት ተቃውሞአቸውን አቀረቡ፡፡
ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ተቃውሞአቸውን የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረቡት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ ምክንያታቸውም ደግሞ በተመሠረተባቸው የሙስና ክስ ላይ ላቀረቡት የክስ መቃወሚያ፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የመቃወሚያ መቃወሚያ ለማቅረብ ሦስት ወራት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ ነው፡፡ 
የክስ መቃወሚያቸውን ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው አቶ መላኩና አቶ ገብረዋህድን ጨምሮ 18 ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ የፈቀደላቸውን ጊዜ ተጠቅመው ሁሉም አቅርበዋል፡፡
በመሆኑም የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ አስተያየቱን ለየካቲት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ሲያሳስብ፣ ዓቃቤ ሕግ ጊዜ እንደማይበቃው ይገልጻል፡፡
ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ከ66 በላይ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመቃወሚያ መቃወሚያ ማቅረብ እንደማይችል በመግለጽ፣ የሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ 
የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ እንደሚቆጠር፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ ዜጐች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን እንደሚያሳጣቸው የተደነገገ መሆኑን በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን የሦስት ወራት ጊዜ ተጠርጣሪ ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት ተቃውመዋል፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአንድ ዓቃቤ ሕግ ይሠራል ተብሎ እንደማይጠበቅና ክሱን ያዘጋጀው ራሱ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሹን አዘጋጅቶ ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ክሱ ከተመሠረተ ከስድስት ወራት በላይ እንደሆነውና በምርመራ ወቅትም ረጅም ጊዜ መውሰዱን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊሰጥበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከጠየቀው ጊዜ በፊት የማይደርስ ከሆነም፣ ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች የቀረበውን ጥያቄ ካዳመጠ በኋላ፣ ተጠርጣሪ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን የሦስት ወራት ጊዜ ወደ አንድ ወር ዝቅ አድርጐ፣ የመቃወሚያ መቃወሚያውን መጋቢት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲያቀርብ አዟል፡፡ ተከሳሾች ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ፍርድ ቤቱ ያለው ነገር የለም፡፡ 
source:http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment