Saturday, February 1, 2014

ንግድ ባንክን ዘርፈዋል የተባሉ ሠራተኞች በምርመራ ላይ ናቸው

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጠገብ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ፣ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ በሠራተኞቹ ባለፈው ሳምንት ውስጥ መዘረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ተጠርጣሪ ሠራተኞች በምርመራ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ተጠርጣሪ ሠራተኞቹ ገንዘቡን ዘርፈዋል የተባሉት ከተቀማጭ ሒሳብ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፣ ገንዘቡ የማይንቀሳቀስ በመሆኑ እንዲንቀሳቀስ  ማድረግ የሚችሉት የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጁ ወይም ምክትል ሥራ አስኪያጁ መሥፈርቶችን በማሟላት በፊርማ ማፅደቅ ሲችሉ ብቻ መሆኑን አክለዋል፡፡
ኃላፊው ገንዘቡ እንዲንቀሳቀስ በፊርማው ካረጋገጠ በኋላ መንቀሳቀስ እንደሚጀምር ምንጮች ገልጸው፣ ተጠርጣሪ ሠራተኞቹ ዝርፊያውን ፈጽመዋል የተባለው ሒሳቡ በመንቀሳቀሱ ነው ብለዋል፡፡ የአስቀማጩን ፊርማ በማጥናትና አመሳስሎ በመፈረም ወደ ራሳቸው አካውንት በማስገባት ወይም በቀጥታ ወጪ በማድረግ ዝርፊያው ሳይፈጸም እንዳልቀረ መጠርጠሩንም አክለዋል፡፡
ገንዘቡን ዘርፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አንዲት ኦዲተርና ምክትል ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ተጠርጣሪ ሠራተኞች ታስረው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 
ተመሳሳይ የዝርፊያ ድርጊቶች በወላይታ ቅርንጫፍና በፊንፊኔ ቅርንጫፍ መፈጸማቸውም ተሰምቷል፡፡ አንድ የወላይታ ቅርንጫፍ ሠራተኛ በዲስትሪክት ኃላፊው ከሥራ ገበታቸው የተባረሩ ቢሆንም፣ በባንኩ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ 
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በተጠርጣሪ ሠራተኞች ተዘርፏል ስለተባለው ገንዘብና በቁጥጥር ሥር ውለዋል ስለተባሉት ተጠርጣሪ ሠራተኞች ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የባንኩን ኃላፊዎች ለማነጋገር ተሞክሯል፡፡ ድርጊቱ መፈጸሙ እውነት መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ በሕግ የተያዘ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የባንኩ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 
ከአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ተዘርፏል የተባለው የገንዘብ መጠን እስከ 10 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይገመታል ቢባልም፣ በትክክል ይህን ያህል ነው ተብሎ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ስለ ጉዳዩ መረጃ ያላቸው የባንኩ ኃላፊዎችም ዝምታን መርጠዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ የሚመራ የባንኩ የዲስትሪክት ሥራ አስኪያጆችን፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶችንና ዳይሬክተሮችን ያካተተ ቡድን ከጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ በባንኩ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ላይ እየተወያየ መሆኑ ታውቋል፡፡
የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን መጨመሩንና በበጀት ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ጥሩ መሠራቱን በማውሳት ስብሰባው በምሥጋና መጀመሩም ተሰምቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪን በሚመለከት በተደረገው ውይይት ችግሩ ሊቀረፍ አለመቻሉንና አሁንም እጥረት መኖሩን፣ ያልተወራረዱ ሒሳቦች በብዛት መኖራቸውን፣ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሒሳብ እንዳለ መጠቀሱንና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን በስብሰባው ከተሳተፉ የባንኩ ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ስብሰባው ጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ማምሻውን ወይም በነጋታው ከቀትር በፊት እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡
source:www.ethiopianreporter

No comments:

Post a Comment