Saturday, February 1, 2014

የቀድሞው የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

በሥልጣን ያላግባብ የመገልገል ወንጀል ተጠርጥረው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝረብ ከመካተታቸው በተጨማሪ ከእህታቸው፣ ከወንድማቸውና የቅርብ ጓደኛቸው መሆናቸው ከተገለጹ ግለሰብ ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው በመከራከር ላይ የሚገኙት፣ የቀድሞው የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤልና ሌሎች ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ሐሳብ ውድቅ ተደረገ፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ እየተመለከተ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 22 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ብይን እንዳስታወቀው፣ ተጠርጣሪዎቹ ላቀረቡት የክስ መቃወሚያ ሐሳብ ከሳሽ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የመቃወሚያ መቃወሚያ ሐሳብ፣ ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹን የተጠርጣሪዎች የክስ መቃወሚያ ነጥቦች ማስተባበል በመቻሉ መቃወሚያውን እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡ 
በመሆኑም በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማንቀሳቀስ በሚል የቀረበው 11ኛ ክስ ለተጠርጣሪዎች ግልጽ ባለመሆኑ፣ የመከላከል መብታቸውን እንደሚያጣብብ በመግለጽ በመቃወማቸው፣ ፍርድ ቤቱም ያመነበት መሆኑን በመግለጽ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር በመግለጽ አሻሽሎ እንዲያቀርብ በማዘዝ ለጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ጋር ተጠርጥረው የተከሰሱትና በእስር ላይ የሚገኙት ወንድማቸው አቶ ዘርዓይ ወልደ ሚካኤል፣ እህታቸው ወ/ት ትርሐስ ወልደ ሚካኤልና የቅርብ ጓደኛቸው አቶ ዱሪ ከበደ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
source:www.ethiopianreporter

No comments:

Post a Comment