Saturday, February 15, 2014

ገናዦቹ:የክፍሉ ሠራተኞች አረንጓዴ ጋዋናቸውን ለብሰዋል፡፡ አፍንጫቸውንም ሸፍነዋል፡፡ ቦቲ ተጫምተዋል፡፡

ከረፋዱ አራት ሰዓት ሆኗል፡፡ የክፍሉ ሠራተኞች አረንጓዴ ጋዋናቸውን ለብሰዋል፡፡ አፍንጫቸውንም ሸፍነዋል፡፡ ቦቲ ተጫምተዋል፡፡ ከክፍሉ የሚወጣው ጠረን አላወካቸውም፡፡ የመጣላቸውን እንግዳ ሊሸኙት ሽር ጉድ ይላሉ፡፡ 
ገናዦቹ
ባለጉዳይ የሚያስተናግዱበት ክፍል ግድግዳ ላይ ሃይማኖታዊ ምሥሎችና ቁሶች ተሰቅለው ይታየሉ፡፡ ከዚህች ክፍል ትይዩ የሚታየው በር ለእንግዳ ክብድ ያለ ስሜት ወደሚፈጥረው ሰፊ ክፍል ማስገቢያ ነው፡፡ 
እርጥብ እጁን እየዘረጋ ቁጡ በሆነ ፊቱ ሰላምታ ሰጠን፡፡ የሥራውን ባህሪም ይበልጥ እናጤነው ዘንድ ወደ ውስጥ እንድንገባ ጋበዘን፡፡ በምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል አስክሬን ክፍል ውስጥ በነጭ ሴራሚክ ወደ ላይ ከፍ ተደርጐ የተሠራው ገንዳ መሳይ የአስክሬን ማጠቢያ በደም ተለውሶ ይታያል፡፡ ይህንን ክፍል አልፈን ወደሚቀጥለው ክፍል ገባን፡፡ የሰላም እንቅልፍ እስከወዲያኛው ያሸለባቸው የሰው ልጆች በሰፊው በተዘረጋላቸው የጣውላ ጠረጴዛ ተደርድረው ይታያሉ፡፡ የመኖርን ከንቱነት በሚመሰክር አተያይ እየተመለከትን ‹‹ይኸው ነው በቃ›› አለ በምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የአስክሬን ክፍል ሠራተኛ የሆነው ነጋሽ አበራ፡፡
ለአሥራ ሰባት ዓመታት ያህል በአስክሬን ገናዥና መርማሪነት በሠራው ነጋሽ ገለጻ ሥራው በጣም አሰቃቂ ነው፡፡ ጭንቀት ይበዛዋል፡፡ ወደ ሥራው ለመጀመርያ ጊዜ በተቀላቀለበት ወቅትም አእምሮው እረፍት አጥቶ ነበር፡፡ ስለዚህም ቀን በሥራ የደከመ ጐኑን ለማሳረፍና ጭንቀቱን ለማስወገድ መጠጣት ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ አስቸጋሪውን የክፍሉን ጠረንና እንዳልነበረ ሆኖ የሚመጣውን በድን የሰው ገላ በትንሹም ቢሆን ተላመደው፡፡ የሕፃናት አስክሬን በሚመጣበት ሰዓት ግን ዛሬም ቢሆን ውስጡ ይረበሻል፡፡ ‹‹ሕፃናት ወንጀል ተፈጽሞባቸውና አደጋ ደርሶባቸው ነው የሚመጡት፡፡ ብዙ ጊዜም ታፍነው፣ ተደብድበውና የመኪና አደጋ ደርሶባቸው ይሞታሉ፡፡ በየቀኑም ከሁለት እስከ አራት ሕፃናት በተመሳሳይ ሁኔታ ሕይወታቸው በማለፉ ወደ አስክሬን ክፍል ይመጣሉ›› በማለት ከሰብዓዊነት ባለፈ የሁለት ልጆች አባት በመሆኑም የሕፃናት አስከሬን እንደሚረብሻቸው ይናገራል፡፡
ከሥራው ክብደትና በሙቀት ሰዓት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን ከመሸሽ አንፃር አስክሬን የማጠብ፣ የመገነዝና የመመርመር ሥራዎችን የሚያከናውኑት በጥዋቱ ክፍለ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በቀን የሚያስተናግዱት አስክሬንም እስከ 20 ሊደርስ ይችላል፡፡ 
ልናነጋግራቸው በሄድንበት ወቅት ከተቀበሏቸው 16 አስክሬኖች መካከል ሁለቱ ወንጀል ተፈጽሞባቸው የሞቱና ፖሊስ መረጃን ለማጠናቀር ሲል ግብአተ መሬታቸው ከተፈጸመ ከወር በኋላ አስወጥቶ ያመጣቸው ናቸው፡፡ ከክፍሉ ከመድረሳችን ጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞ ደግሞ ከተቀበረች ከወር በላይ የሚሆናት የአንዲት ወጣት ቅሪተ አካል መጥቶ ሲመረምሩት እንደቆዩ አቶ ነጋሽ ገልጿል፡፡ 
ነጋሽ በዚህ ሥራ ላይ በየቀኑ የሚፈጠሩ ገጠመኞች አሉት፡፡ ‹‹የክፍሉ ሠራተኞች ውስን በመሆናችን ሥራ ይበዛብናል፡፡ በዚህ መካከል ደግሞ አለቃችን መቅረት በማብዛቱ ችግራችን ተባብሶ ነበር፡፡ አንድ ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ አንገቱን በቢላ ቀልቶ ይሞታል፡፡ አስክሬኑን ወደ እኛ ያመጡታል፡፡ የተለመደ ሥራችንን ለማከናወን በጨርቅ የተሸፈነውን አስክሬን ብንገልጠው እዚሁ ክፍል አብሮን አስክሬን በመመርመር፣ በመገነዝና በማጠብ የሚሠራው አለቃችን በድን ፍጥጥ ብሎ አገኘነው›› በማለት ከዓመታት በፊት የገጠመውን ያስታውሳል፡፡ 
ወንጀል ተፈጽሞባቸው ሕይወታቸው በሚያልፍ ሰዎች ላይ ፖሊስ የሚያደርገውን ክትትል ለማደናቀፍ ዱካ ለማጥፋት ሲሉ ብቻ ወደ አስክሬን ክፍሉ በመምጣት ያልሆነ መረጃ የሚሰጡ ወንጀለኞች መኖራቸውም አንዱ የአስክሬን ክፍሉ ገጽታ እንደሆነ ይናገራል፡፡ 
ነጋሽ ከዚህ ሥራ ለመላቀቅ ብዙ ቢጥርም አልተሳካለትም፡፡ ሥራውን ደፍሮ የሚሠራ የሰው ኃይል ባለመኖሩም የአስክሬን ክፍሉ ሥራ በአራት ሰዎች ጫንቃ ላይ አርፏል፡፡ ከመቀሌ ውጭ ከሁሉም አካባቢዎች ለምርመራ የሚመጣ አስክሬን የመመርመር፣ አስተካክሎና ገንዞ የመመለስ ግዴታ አለባቸው፡፡ እንደ ሌላው የሆስፒታሉ ሠራተኞች የዓመት ፍቃዳቸውን ለመውጣት ሥራውን የሚሠራ ሌላ የሰው ኃይል ባለመኖሩ የዓመት ፍቃዳቸው በገንዘብ ተቀይሮ እንደሚሰጣቸው ይናገራል፡፡ 
በሚያገኛት ዝቅተኛ ደመወዝ ራሱንና ቤተሰቡን ማኖር ባለመቻሉ ሌሎች ተጨማሪ በራሪ ሥራዎችን በትርፍ ሰዓቱ በመሥራትም ኑሮን ይገፋል፡፡ 
‹‹ለመኖራችን ዋስትና የሌለን ፍጡሮች ነን፡፡ ስለወደፊት መጨነቅ የለብንም፡፡ ጊዜአችን አሁን ነው፡፡ በዚህም ጥሩ ሥራ ሠርተንና ተደስተን ማለፍ አለብን፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ቀናችን ሊሆን ይችላል፡፡ ልንሞት እንችላለን›› በማለት ቀና ብሎ ክፍሉ ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሥዕሎች አየ፡፡ በማከልም ‹‹ጭንቀታችንን የምናስወግደው ሥራ ከመጀመራችን በፊት ወደ ቢሮ ስንገባ፣ ስንወጣና ስንተኛ ወደ ፈጣሪ በመጸለይና በማመስገን ነው›› አለ፡፡ 
በምኒልክ ሆስፒታል የአስክሬን ጫኝና አውራጅ የሆነው ሰለሞን ኃይሌ በዚህ ሙያ ለ14 ዓመታት ያህል አገልግሏል፡፡ ወደዚህ ሥራ ከመምጣቱ በፊት ጋምቤላ በሱርማ አካባቢ ከቤተሰቦቹ ጋር ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ወላጆቹን የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን ሳያገባድድ ሞት ነጠቀው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ራሱን ለመቻል ትምህርቱን አቋርጦ የመኪና ረዳት በመሆን በሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ኑሮውን ይመራ ጀመር፡፡ ነገር ግን ከዓመታት በፊት በጋምቤላ አካባቢ በተነሳው የእርስ በርስ ግጭት ትውልድ ሥፍራውን ጥሎ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ 
ከአራት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በምኒልክ ሆስፒታል በአስክሬን ጫኝና አውራጅነት መሥራት ጀመረ፡፡ እሱ እንደሚለው ወርኃዊ ደመወዝ የላቸውም፡፡ የሟች ቤተሰቦች አስክሬኑን ለማውረድና ለመጫን በሚከፍሏቸው በአስክሬን 25 ብር ይኖራሉ፡፡ 
አስክሬን ከመኪና ላይ ማውረድ ስትጀምር የድንጋጤ ስሜት አይሰማህም? ስንል ሰለሞንን ጠየቅነው፡፡ ፊቱን በፈገግታ አድምቆና በጠቋሚ ጣቱ ጭንቅላቱን እየነካ ‹‹እኛ’ኮ መደንገጫችን ተበላሽቷል፡፡ እንዴት እንደነግጣለን›› ሲል መልሶ እኛኑ ጠየቀን፡፡ በሥራው ለዓመታት በመቆየቱ የተለየ ስሜት የማይሰማው ቢሆንም በአሰቃቂ አደጋዎች ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ሲገጥሙት እንደሚዘገንነው ተናግሯል፡፡
ከዓመታት በፊት በሱሉልታ አካባቢ ነዳጅ ጭኖ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቦቴ በመቃጠሉ ለአደጋው ተጋላጭ የሆነ ግለሰብ የደረሰበትን ከባድ አካላዊ ጉዳት ተመልክቶ በተፈጠረበት ያለመረጋጋት ስሜትና የመቃዠት ሁኔታ ለሁለት ዓመታት ያህል ፀበል ገብቷል፡፡ አስክሬን እንዲያነሳ በተላከበት ወቅት አብሮት የዋለውን ጓደኛው አስክሬን ሆኖ አግኝቶትም ለተወሰነ ጊዜ ሥራውን እንዳቆመ ያስታውሳል፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ወቅት በአካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ በደም የራሰ ወጣት ድንገተኛ ክፍል ገብቶ ሲመረመር መሞቱ በመረጋገጡ በመኪና ተጭኖ ወደ አስክሬን ክፍል ይላካል፡፡ ሰለሞንም እንደለመደው የተጫነውን አስክሬን ለማውረድ በተጠጋው ጊዜ ያልተለመደ ክስተተ ያጋጥመዋል፡፡ ሕይወቱ እንዳለፈ የተረጋገጠው ወጣት ግራ የተጋቡ ዓይኖቹን ቁልጭ ቁልጭ እያደረገ በሕይወት መገኘቱን ይገልጻል፡፡ 
በክፍሉ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችን ሁሉ በእምባ ያራጨ አጋጣሚም እንደነበር አጫውቶናል፡፡ ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት በኮልፌ ልኳንዳ 18 አካባቢ ኮንቴነር ጭኖ ሲበር የነበረ መኪና በደረሰበት አደጋ የጫነው ኮንቴነር ሰዎች ላይ በመወደቁ ብዛት ያላቸው ሰዎች ሕይወታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ያልፋል፡፡ አስክሬናቸውም ተጭኖ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ይላካል፡፡ 
ሰለሞንና ጓደኞቹ እንደወትሮ ሥራቸውን ማከናወን ተሳናቸው፡፡ ትራፊክ ፖሊሶችም ያነባሉ፣ በአካባቢው ያለ ሰው ሁሉ ተረብሿል፡፡ አንጀታቸው ደንዳና የሆነው እነ ሰለሞንና መላው የአስክሬን ክፍል ሠራተኛ እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ በወቅቱ ሕይወታቸው ካለፈ ግለሰቦች መካከል ሕፃናትም ይገኙበታል፡፡ አብዛኞቹ አደጋው እንዳልነበሩ አድርጐ ስለጐዳቸው ፆታቸውን መለየት እንኳ ይከብድ ነበር፡፡ በዚህም በጣም ተረብሸው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ 
አልፎ አልፎም ሞቷል ተብሎ በሳጥን ተጭኖ የመጣ አስክሬን ድንገት ሲከፈት እጁ ተወርውሮ በመውጣት እንደሚነካቸውና ደንግጠው የሚሮጡበት ጊዜ ጥቂት እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ 
የሥራ ጫናው የምኒልክ ሆስፒታልን ያህል ባይሆንም ስሙን በማንገልጸው ሆስፒታል የአስክሬን ክፍል የሚሠሩትን ሰዎችም ለማነጋገር ሞክረን ነበር፡፡ በተለመደው ቁጡ አነጋገር የተቀበሉን የአስክሬን ክፍል ተቆጣጣሪ ጐልማሳ ናቸው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ በክፍሉ የሚሠሩ ብዙዎቹ ስለሥራው ከማውራት ይልቅ ‹‹ሥራው በቃ ሥራ ነው ምንም የተለየ ነገር የለውም›› ማለትን መርጠዋል፡፡ 
ማንነቱ እንዲገለጽ ያልፈለገው የ31 ዓመት ወጣት ሊያናግረን ፈቀደ፡፡ ቤተሰብ መሥርቶ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነው፡፡ በአስክሬን ክፍል ውስጥ መሥራት ከጀመረ ዓመት አልፎታል፡፡ ሥራውን በጀመረበት ወቅት ያለመረጋጋት ይታይበት ነበር፡፡ በተለይም ሌሊት ላይ እንደሚቃዥና እንደሚባንን ይናገራል፡፡ ይህ ሁኔታ እየቆየ ቢተወውም ቆየት ካለ አስክሬን የሚወጣው መጥፎ ጠረን ከኬሚካል ጋር ተደባልቆ የሚፈጥረው አስከፊ ሽታ ያውከዋል፡፡ ይህንንም ለማስተካከል በሚል ብዙ ጊዜ ሻይ በሎሚ ይጠጣል፡፡ 
እሱ እንደሚለው ሊረብሹ የሚችሉ አጋጣሚዎች ጥቂት አይባሉም፡፡ ‹‹አስከፊ አደጋ ደርሶባቸው ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ማየት በራሱ ውስጣችንን ያመዋል፡፡ አልፎ አልፎም ስሜቱ የተጐዳ የሟች ቤተሰብ ሕሊናችንን የሚጐዳ ንግግር ይናገረናል፡፡ በአንድ ወቅትም ሀዘን የጐዳው የሟች ቤተሰቦች አስክሬን ሊወስዱ መጥተው ‹አንተ ነህ የገደልከው› ብለውኛል›› ይላል፡፡ ከዚህ ሥራ ለመላቀቅ በማሰብም የቪዲዮና ፎቶ ጥበብ ይማራል፡፡ 
በአስክሬን ክፍል መሥራት የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በ6 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት የሁለተኛ ዓመት የማስተርስ ዲግሪ ተማሪ የሆነችው መዓዛ አብርሃም ይህንኑ ሐሳብ ትደግፋለች፡፡ እሷ እንደምትለው ብዙ ሰው ሞት እንዳለ ቢያውቅም በሕይወት የመኖር ፍላጐት አለው፡፡ ስለዚህም ስለሞት በሰማ ቁጥር ይጨንቀዋል፡፡ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ደግሞ በአስክሬን ክፍል የሚሠሩ ሰዎች በድን ከሆነ አካል ጋር ብዙ ሰዓት አብረው በማሳለፋቸው ሞት የማይሸሹት እውነት መሆኑን ከሌሎች በበለጠ ይረዱታል፡፡ በዚህም ፍርኃት፣ ደስተኛ አለመሆንና ሕይወት ትርጉም ያጣባቸዋል፡፡ በመሆኑም ለነገሮች ግድ ማጣትን ያስከትልባቸዋል፡፡ ይህም ለተወሰነ ወቅት ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም የሚከፈላቸው ወርኃዊ ደመወዝ ማነስ፣ ኅብረተሰቡ ለእነርሱ ያለው ግምትና ወደ አፈር ሊቀላቀል (የሚጣል) አካል በማዘጋጀት ላይ በመሆናቸው ዋገ ቢስነት ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የሚያበረክቱት በጐ ነገር ያለ መስሎ ላይሰማቸው እንደሚችል መዓዛ ትናገራለች፡፡ 
ይሁን እንጂ ይህን ስሜት ላይሰማቸው የሚችል ሰዎችን ማግኘት በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችልና ቢኖሩም ሲበዛ በጐ አሳቢ መሆን አለባቸው፡፡ ስለዚህም የሚሠሩት ሥራ ብዙ ሰው የማይሠራው በመሆኑ ኩራት ሊሰማቸው ይችላል፡፡                                   
       

No comments:

Post a Comment