Thursday, February 6, 2014

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር «ኦሮሞዉን» ጎድቷል - አማኑኤል ዘሰላም

የኢትዮጵያ ፈዴራል ሕገ መንግስት አንቀጽ 46 «ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነዉ» ይላል። አንቀጽ 47 ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሩፑብሊክ አባላት የሆኑቱን ክልሎች ይዘረዝራቸዋል። እነርሱም የትግራይ፣ የአፋር ፣ የአማራ፣ የሱማሌ፣ የቤኔሻንጉል/ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች እና የሃረሪ ሕዝብ ክልሎች ናቸው።
የዚህን የፌደራል ክልልን በተመለከተ በክልሎች እየታዩ ያሉትን አንዳንድ ሁኔታዎች ለማሳየት እንሞክራለን። ከትልቁ ክልል ኦሮሚያ እንጀምር።
Oromiaኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ሃያ ዞኖች አሉ። ሶስቱ «ልዩ ዞኖች» ይባላሉ። ናዝሬት/አዳማን ያካተተ፣ የአዳም ልዩ ዞን፣ ጂማን ያካተተው፣ የጂማ ልዩ ዞን እና የቡራዮ ልዩ ዞን ናቸው። በነዚህ ዞኖች የመጀመሪያ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑቱ ቁጥራቸው ከ45 በመቶ በታች ነዉ። በአዳማ 26%፣ በጂማ 39% እና በቡራዮ 44% ናቸው።

በአሥራ ሶስቱ ሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች አፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ቋንቋቸው የሆኑ ከ90 % በታች ናቸው። እነዚህም ምስራቅ ሸዋ ( 69%)፣ ጉጂ (77%) ፣ አርሲ ( 81%)፣ ሰሜን ሸዋ ( 82%)፣ ደቡብ ምስራቅ ሸዋ (84%)፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ (85%) ፣ ምእራብ አርሲ (87%)፣ ምስራቅ ወለጋ (88%) ፣ ምእራብ ሃረርጌ (89 %)፣ ኢሊባቡር (90%) ፣ ጂማ – የጅማ ከተማ አካባቢ ( 90%)፣ ባሌ (90%)፣ ቦረና (90%) ናቸው። እንግዲህ ከሃያ የኦሮሚያ ዞኖች፣ በአሥራ ስድስቱ፣ ምን ያህል አፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ያልሆኑ ኢትዮጵያዉያን በስፋት እንዳሉ እያየን ነዉ። በአራት የኦሮሚያ ዞኖች፣ በአፋን ኦሮሞ አፋቸዉን የፈቱ፣ ከዘጣና ሶስት በመቶ በላይ ናቸው። እነርሱም ምእራብ ወለጋ (97%) ፣ ምእራብ ሸዋ (93%)፣ ምስራቅ ሃረርጌ፣ (94%)፣ ቀለም ወለጋ ( 94%) ናቸው።

አሁን በሥራ ላይ እየተተገበረ ያለው የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ 33 «በክልሉ ዉስጥ ነዋሪ የሆኑና የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በማንኛዉም የክልሉ መንግስታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ ወይም ተቀጥሮ የመስራት መብት አለዉ።» ይላል። አንቀጽ 5 ደግሞ « ኦሮምኛ የክልሉ መንግስት የሥራ ቋንቋ ይሆናል። የሚጻፈዉም በላቲን ፊደል ነው» ይላል።
74% የአዳማ፣ 61% የጂማ ከተማ ፣ 56% የቡራዩ ዞን፣ 31% የምስራቅ ሸዋ ዞን፣ 23% የጉጂ ዞን ፣ 25% የሆሮ ጉድሮ ወለጋ ዞን፣ 23% የምእራብ አርሲ ዞን … ነዋሪዎች የመጀመሪያ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ ባላመሆኑ፣ አፋን ኦሮሞ ካልተማሩ በቀር፣ የመመረጥ፣ በኦሮሚያ ክልል የመስራት መብት የላቸውም። ይህም አማርኛና ሌሎች ቋንቋዎች የሚናገሩ፣ በኦሮምያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ የሚያደርግ ነዉ። በብሄረሰብ መብት ስም የግልሰበ መብት እየተረገጠ ነዉ።
«ኦሮሚያ ፈርስት» የሚል እንቅስቃሴን የሚመራው ጃዋር ሞሃመድ፣ አንድ ወቅት «Ethiopians Out from Oromia» የሚል መፈክር ያሰማበትን ቪዲዮ ተመልክቻለሁ። ጃዋር በአጭሩ አነጋገር፣ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ እንደሆነችና ሌሎች «ኦሮሞ» ያልሆኑ፣ በኦሮሚያ ዉስጥ እንግዶች፣ ኦሮሞዎች ሲፈቅዱላቸው ብቻ ሊኖሩ የሚችሉ እንደሆኑ ነው የነገረን። ይህ የጃዋር አባባል፣ ብዙዎችን እንዳስገረመ ተመልክቻለሁ። ነገር ግን አንድ የዘነጋነው ነገር ቢኖር፣ ይህ የጃዋር አባባል ፣ ጃዋር የፈጠረዉ ሳይሆን በኦሮሚያ በአሁኑ ሕግ መንግስት፣ በሰነድ የተቀመጠ እንደሆነ ነዉ።ይህ አይነቱን ዘረኛ የጃዋር አባባል፣ የኦሮሚያ ክልል «ሕግ» ይደግፈዋል።
የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ ስምንትን ይመልከቱ። «የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ስልጣን ባለቤት ሲሆን ..» ሲል የኦሮሚያ ባለቤት «ኦሮሞው» ብቻ እንደሆነ ነው የተቀመጠው።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ፖሊሲን ካየን ደግሞ፣ አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ እንደ አዳማ/ናዝሬት ያሉ ቦታዎች ሕዝቡ ተቃዉሞ ስላስነሳ፣ በዚያ ተማሪዎች አማርኛም ከአፋን አፋን ኦሮሞ ጎን ለጎን እንዲማሩ ከመደረጉ በስተቀር፣ በኦሮሚያ የሚኖሩ ተማሪዎች አማርኛ እንዲማሩ አይደረግም። አማርኛ ማንበብና መጻፍ አይችሉም።
አንድ የግል ባለሃብት ከአዲስ አበባ ሄዶ አንድ ኩባንያ በአንድ የኦሮሚያ ከተማ ይመሰርታል። ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል። ሰራተኞቹ ስራቸዉን በተመለከተ፣ ሪፖርት ማቅርብ ሲጠበቅባቸው ሪፖርት ሳያቀርቡ ይቀራሉ። አለቃቸው ያስጠራቸዉና ይጠይቃቸዋል። ሪፖርታቸውን በቃል ያቀርቡለታል። «እሺ በፋይል እንዲቀመጥ በጽሁፍ አምጡልኝ» ሲላቸው፣ ማንገራገር ጀመሩ። «ጌታዬ እኛ አማርኛ መጻፍ አንችልም። በቁቤ እንጻፈዉና ከፈለጉ ያስተርጉሙት፤ ወይም እኛ አስተርጉመን እንመጣለን» ይሉታል። ሰዎዬዉ ባንድ በኩል በጣም ተናደደ፣ በሌላ በኩል አዘነ። ቢዝነስ ነዉና፣ ለስራው ብቃት ከሌላቸው ሰራተኞቹ መባረር አለባቸው።
አማርኛን የመጥላት የኦህደድ እና ኦነግ ፖለቲካ ፣ ዜጎች አፋን ኦሮሞን ያዉም በቁቤ ብቻ እንዲማሩ በማድረግ፣ ትልቅ የኢኮኖሚ ጉዳት በ«ኦሮሞዎች» በትግራይ ከአንደኛ ክፍል ጀመሮ ከትግሪኛ ጎን አማርኛ እንዲማሩ ይደረጋል።
የኦሕደድ ባለስልጣናት እነ አባ ዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ የመሳሰሉት ልጆቻቸዉን የሚያስተምሩት በአዲስ አበባ ሃሪፍ ተምህርት ቤቶች ነዉ። ሃብታም የሆኑና አቅሙ ያላቸው ልጆቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እየላኩ ያስተምራሉ። ለምን ቁቤ ብቻ ተምረው ልጆቻቸው የትም እንደማይደርሱ ስለሚያወቁ።
የግል ኢንቨስተሮች የሥራ ቋንቋቸው በኦሮሚያም ሳይቀር በብዛት አማርኛ ነዉ። በናዝሬት፣ በጂማ በመሳሰሉት ቦታዎች ሂዱ፣ የንግድ ተቋማት፣ የግል መስሪያቤቶች .. የሚጠቀሙት አማርኛን ነዉ። ከክልል መንግስት ጋር አንዳንድ ደብዳቤዎች መላላክ ካስፈለገ ፣ የክልሉን የአፋን ኦሮሞ ብቻ ፖሊስ ሕግን ለማክበር ፣ ተርጓሚ ይቀጥራሉ።
በኢትዮጵያ ካሉ 9 ክልሎች በአራቱ (አማራዉ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ) ክልሎች፣ እንዲሁም በአገሪቷ መዲና አዲስ አበባ፣ በድሬደዋ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው። የፌደራልም ቋንቋ አማርኛ ነዉ።
በመሆኑም ኦሮሚያ ያለው የቁቤ ትዉልድ፣ በፌደራል መንግስት ዉስጥ ተቀጥሮ የመስራት አቅሙ ዜሮ ነዉ። እንደ ባህር ዳር፣ አዋሳ፣ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ታላላቅ ከተሞች ለመኖርና ለመስራት፣ ለመቀጠር በጣም ይቸገራል። በአጭሩ በኢኮኖሚ እንያድጉና እንዳይሻሻሉ ትልቅ ማነቆ ነው እየሆነባቸው ያለዉ ይህ የኦሮሚያ ክልል አሰራር። በሌሎቹ ክልል ካሉ ጋር ሲወዳደሩ ወደኋላ ቀርተዋል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የኦነግ መሪዎች ልጆቻቸው በበርሊን ሚኒሴቶች …በመሳሰሉ ቦታዎች ናቸዉ። አማርኛም ባያወቁ፣ እንግሊዘኛ እስካወቁ ድረስ ችግር አያጋጥማቸዉም። የኦህደድ መሪዎች ልጆቻቸውን ሃሪፍ ትምህርት ቤቶች ነዉ በአዲስ አበባ የሚያተምሩት። ድሃዉና ምስኪኑ የኦርሚያ ተማሪ ግን፣ አጥር ታጥሮበት፣ በአጉል የኦሮሞ ብሄረተኘንት ስም እንዲተበተብ ተደርጎ ጉዳት እየደረሰብት ነዉ።
ይህ በኦሮሚያ የሚኖረው ወገናችን በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ፖሊሲ ረገድ እየደረሰበት ካለው ግፍ በተጨማሪም፣ ኦነግ እየተባሉ በሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እየታሰሩና እየተሰቃዩ ናቸው። ሕወሃት/ኢሃዴግ በአንድ በኩል እነሌንጮን ቀንደኛ ኦነጎችን እያባበለ፣ በሌላ በኩል የነሌኝቾ ደጋፊ ናችሁ እያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ያስራል።
ታዲያ መፍትሄዊ ምንድን ነዉ ? አራት መፍትሄዎች አሉ፡
1. ኢትዮጵያዉያን አፋቸዉን በየትኛው ቋንቋ ነዉ የፈቱት የሚለዉን ጥያቄ ብንጠይቅ ፣ በአንደኝነት የሚቀመጠዉ ኦሮምኛ ነዉ። በበርካታ ዞኖች ከዘጠና በመቶ በላይ ኦሮምኛ የሚነገርባቸው ቦታዎች አሉ። 33.8 % የሚሆነው ሕዝባችን አንደኛ ቋንቋዉ አፋን ኦሮሞ ነዉ። 29.36% የሚሆነው ህዝብ አማርኛ አንደኛ ቋንቋዉ ነዉ። ሁለቱ ቋንቋዎች እንደ አንደኛ ቋንቋ የሚናገሩ 63.2% ይደርሳሉ። በመሆኑም ኦሮሞኛ ከአማርኛ ጎን የፌደራል ቋንቋ ቢሆን ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል።
2. በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች፣ በአካባቢዉ ከሚነገረው ቋንቋ ጎን ለጎን፣ ተማሪዎች አማርኛ እንዲማሩ መደረግ አለበት። አማርኛ እንደ አንደኛ ቋንቋ 29.3% የሚሆነው ሕዝብ ይናገረዋል። እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ደግሞ፣ ከ30፣ 40 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ሊናገረው ይችላል ብዬ አስባለሁ።በመሆኑም አማርኛ ማወቅ ጥቅም አለው። ቋንቋ በአጠቃላይ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። አማርኛን መማር ኦሮሞኛን አይጎዳም። የኦሮሞ መሪ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች፣ ለራሳቸው ልጆች እንዳሰቡት፣ ለተቀረዉም የኦሮሞ ልጅ ሊያስቡ ይገባል ባይ ነኝ።
3. የኦሮሚያ ክልል መንግስት አማርኛን ከኦሮሞኛ ጎን የሥራ ቋንቋ ማድረግ አለበት። ኦሮሞኛ የማይናገር በክልሉ አስተዳደር ዉስጥ የመስራት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። በኦሮሚያ 95% ነዋሪዉ ኦሮሞኛ የሚናገር ቢሆን፣ እሺ አንድ ነገር ነዉ። ግን ከ 15% በመቶ በላይ ሕዝብ አንደኛ ቋንቋም ኦሮሞኛ ባልሆነበት፣ «አፋን ኦሮሞ ብቻ ወይንም ሞት» ማለት ትልቅ ስህተት ነዉ። በክልሉ ዋና ከተማ አዳማ/ናዝሬት እንኳን ፣ አንድ አራተኛ ሕዝብ ብቻ ነው ኦሮሞኛ የሚናገረው።
4. ናዝሬት/አዳም እና ጂማ የመሳሰሉ እንደ አዲስ አበባና ድሬደዋ፣ ለጊዜዉ ቻርተር ከተማ ቢሆኑ መልካም ነዉ። (ለዘለኬታዉ፣ ለሁሉም በሚበጅ፣ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባና በተጠና መልኩ ፣ፌደራል አወቃቀሩ እንደገና በአዲስ የሚዋቀርበትን ሁኔታ በመፈለግ ለብዙ ችግሮች መፍቴሄ ማግኘት ይቻላል)
ከላይ የዘረዘርኳቸዉ አሃዞች በኦፊሴል ከተመዘገበዉ የኢትይጵፕያ ሕዝብ ቆጠራ ሪፖርት ነዉ። በሚቀጥለው ጊዜ የቤኔሻንጉል ጉምዝ እና ሃረሪ ክልሎችን እንመለከታለን።
Ze-Habesha Website

No comments:

Post a Comment