Wednesday, February 12, 2014

ከጥቃት ያላመለጡ እንስቶች

‹‹በየሰዓቱ 50 ወጣት ሴቶች በኤችአይቪ ይያዛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በርካቶቹ ለቫይረሱ የሚጋለጡት የሚደርስባቸውን ጾታዊ ትንኮሳ ተከትሎ ነው››
ይላል ከኅዳር 16 – ታኅሣሥ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የሴቶች ጥቃት የማውገዝ ቀን በማስመልከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው መግለጫ፡፡ መረጃው ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆነና ድንበር ሳይለይ ሴቶች ላይ እንደሚፈጸምም ይገልጻል፡፡
ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም በማሳሰብ ቀኑን ካከበሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ሴቶች በመኖሪያ አካባቢ፣ በትምህርት ቤት፣ መሥሪያ ቤት መንገድ ላይ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ‹‹ቆመሽ አናግሪኝ›› ከሚል የቃል ማስፈራሪያ የሚጀምረው ጥቃት እስከ ዓይን ማውጣት፣ መግደል፣ በአሲድ ማቃጠል ይደርሳል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ጉልበት ተጠቅመው ሴቶችን ለመቅረብ ስለሚሞክሩ ወንዶች እንድታነጋግረን ጠየቅናት፡፡ ወደ መኝታ ክፍሏ ጋበዘችን፡፡ ወደ ሴቶች መኝታ ክፍሎች (በተለምዶ ሳይቤሪያ ወደሚባለው) የሚወስደውን መንገድ ይዘን እየሄድን በአቅራቢያው ካለው የወንዶች መኝታ ክፍል አንገታቸውን በመስኮት ያወጡ ወንዶች ‹‹አንቺ የዛፍ ቆራጭ ልጅ ምን ትቅለሰለሺያለሽ፤ ድርያ የለበስሽው የድሬዳዋ ልጅ ለመምሰል ነው? ቀሚስሽ ውስጥ ብቻሽን ከፈራሽ…›› ሌላም በርካታ አፀያፊ ንግግር እየተቀባበሉ ተናገሩ፡፡ ወጣቷ አንገቷን አቀርቅራ ጉዞዋን ቀጠለች፡፡
ሁኔታው ለሷ አዲስ አልነበረም፡፡ ሴቶች ከሚደርስባቸው አካላዊ ጥቃት ጋር ሲነጻጸር በአቋማቸው ከዘራቸው፣ ከባሕሪያቸው፣ ከአለባበሳቸውና ከሚያጠኑት ትምህርት ጋር በተያያዘ በቃላት መተንኮሳቸው በወጣቷ ዓይን ‹‹ቀላል›› ነው፡፡ መንገድ ላይ ጠብቀው ‹‹ደስ ስለምትይኝ ነው›› ብለው ተለሳልሰው የሚጠጉ፣ የሚፈልጉትን የእሺታ ምላሽ ካላገኙ የሚቆጡ፣ ከመነሻውም በጉልበት የሚጠቀሙ ወንዶች በየቀኑ ያጋጥማሉ፡፡ ወጣቷ እንደገለጸችው ትንኮሳው በትምህርትና በማኅበራዊ ሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ቤተ መጻሕፍት ፊት ለፊት ደብተር የያዘች ሴት ሐውልት አለ፡፡ ከረዥም ዓመታት በፊት ‹‹የፍቅር ጥያቄዬን አልተቀበለችም›› በሚል ወንድ በጩቤ ተወግታ የሞተች ሴት መታሰቢያ ነው፡፡ ይህ መታሰቢያ የሚያሳየውም በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃስ እስከ መገደልም የጠነከረ መሆኑን ነው፡፡
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ሌላ ተማሪ እንደነገረችን ልጁ ለረዥም ጊዜ ይከታተላት ነበር፡፡ አንድ ቀን ብቻዋን ያገኛትና እንድታናግረው ያስገድዳታል፡፡ ክንዷን ጨምድዶ የስልክ ቁጥሯን ካልሰጠችው እንደማይለቃት ሲነግራት የተሳሳተ ቁጥር ትነግረዋለች፡፡ በቆመችበት ወደ ሰጠችው ቁጥር ሲደውል የምትገባበት ይጠፋታል፡፡
ስልክ ቁጥሯን እንደዋሸችው አምና እየተለማመጠችው ትክክለኛ ቁጥር አስመዝግባ ትለየዋለች፡፡
በክፍልና በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሳለች፣ ምግብ ስትበላ፣ በውድቅት ሌሊትም እየደወለ እንደሚወዳትና የሴት ጓደኛው ካልሆነች እንደማይተዋት እየወተወተ ሰላም ይነሳታል፡፡ ‹‹ስልኬን ካላነሳሁ በነጋታው የገባሁበት ገብቶ ፈልጐ ያስፈራራኛል፡፡ ለመቆጣት የሞከርኩ ቀን በጥፊ መትቶኝ ያውቃል፡፡ ራሴን መከላከል አልችልም፡፡ ለሌላ አካል ማሳወቅም የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ስልክ ቁጥሬን ቀይሬ የማዘወትርበትን አካባቢም ትቼ ነበር፡፡ ነገር ግን ለቤተሰብና ጥቂት ጓደኞቼ የሰጠሁትን አዲስ ቁጥር አግኝቶ መደወል ቀጠለ፡፡ ከሁለት አንዳችን ተመርቀን እስክንወጣ መፍትሔ ያለው አይመስለኝም፤›› ብላለች፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ባደረገው ጥናት ከሦስት ሴቶች አንዷ ወሲባዊ ትንኮሳ ይደርስባታል፡፡ አግባብ ከጎደለው አነጋገር እስከ ከባድ አካል ጉዳትና ሞት የሚደርሰው ጥቃት በብዙ መድረክ ይኮነናል፡፡ ኅዳር 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በተከበረው የነጭ ሪቫን ቀንም ‹‹የሴቶችን ጥቃት እናስቆማለን›› የሚል መልዕክት ተላልፏል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ለፈተና አንድ ቀን የቀራት ወጣት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እስከ እኩለ ሌሊት ታጠናለች፡፡ አንድ ተማሪ ከጠረጴዛ አልፎ ለማናገር ሲሞክር ትኩረት ሳትሰጠው ንባቧን ትቀጥላለች፡፡ ጥቂት ቆይቶ ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲጠጋት ወደ ሌላ ወንበር ትሄዳለች፡፡ ተከትሏት ከጎኗ ተቀምጦ ድንገት ከቀሚሷ ስር እጁን ሲሰድ በንዴት ጦፋ በጥፊ ስትመታው በቦታው የነበሩት የጥበቃ ኃይሎች ‹‹ቤተ መጻሕፍት ረብሸሻል›› በሚል መታወቂያ መቀማቷን የነገረችን ተማሪም ሩት ነች፡፡
የሴቶችን ጥቃት አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ የሚያልፍ መብዛቱን ተማሪ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ወደ ዩኒቨርሲቲ ስንገባ ማንኛውም ጥቃት ቢደርስብን ከለላ እንደሚደረግልን ቢነገረንም አንዲት ሴት ጥቃት ደርሶብኛል ብላ ብትከስ በቁም ነገር ጉዳይዋን የሚያይላት የለም፡፡ ምስክር አምጪ ትባላለች፡፡ አልፎ ተርፎም ጥፋተኛ ተደርጋ ልትባረር ትችላለች፤›› ትላለች፡፡
በአንድ የግል መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ ነው፡፡ ሴቶችን ጉልበት ተጠቅሞ አናግሮ እንደሚያውቅ ነገረን፡፡ ‹‹አንድ ሴት ደስ ካለችኝ እልህ ይዟት እንደምታናግረኝ ስለማውቅ መጀመርያ እሰድባታለሁ፡፡ ትከሻቸውን ወይም እጃቸውን በኃይል ይዤ አናግሩኝ ብያቸው ያናገሩኝም አሉ፤›› ያለን ወጣት፣ ሴቶች በጉልበት ገፍቶ የሚመጣን ወንድ እንደሚወዱ ያምናል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪው ካሳሁን ለማ ደግሞ በጉልበት የሚመሠረት ግንኙነት መጨረሻው ስለማያምር ተጠቅሞ እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ ‹‹ትምህርት ቤትም ሆነ ሰፈር ውስጥ ሴቶች ላይ ጥቃት ሲደርስ አያለሁ፡፡ እኔን መጉዳት የማይችል ወንድ ከሆነ ለመከላከል እሞክራለሁ፤ አንዳንዴ ግን ዝም ብዬ አልፋለሁ፤›› ብሏል፡፡
‹‹ሴትን እንደ አሻንጉሊት የሚያዩ አሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሱስ የተጠመዱ ወንዶችን እናውቃቸዋለን፡፡ ማታ ማታ ጠጥተው መጥተው በቡድን ተሰብስበው ሲቀመጡ በአጠገባቸው ላለማለፍ መንገድ እንቀይራለን፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተደፈሩ ሴቶችን ታሪክ ስለምንሰማ ከአምስት ሰዓት በኋላ በኅብረት ካልሆነ አንንቀሳቀስም፤›› ያለችው የሕክምና ተማሪ ቤተል ፈቃደ ናት፡፡
ይህ የአይጥና ድመት ድብብቆሽ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ይታያል፡፡ በየካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ብሌን ገንዘቤነህ የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ያጋጠማትን ገልጻለች፡፡ በትምህርት ቤት የምታውቀው ልጅ የፍቅር ጥያቄ ያቀርብላታል፡፡ እስከ ሰፈሯ ድረስ ይከተላት ስለነበረ ትስማማለች፡፡ ‹‹ብዙ ሴቶች እምቢ በማለታቸው ሲደበደቡ አይቻለሁ፡፡ እሺ ብዬ ራሴን ካዳንኩ በኋላ በሚግባባቸው ልጆች በኩል ፍላጎት ስለሌለኝ እንዲተወኝ አስለመንኩት፡፡ መጀመሪያ አቅማማ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ከትምህርት ቤቱ ለቀቀ፤›› ብላለች፡፡
በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ‹‹ቁሚ›› የሚል ቃል ከሰሙ ቀጥ ብሎ ከመቆም ሌላ አማራጭ እንደሌለ የተናገረችው የ18 ዓመቷ አዲስዓለም ናት፡፡ በክፍል ከፍ ያሉ ወንዶች ሴቶችን እንዳሻቸው ማድረግ የሚችሉ እንደሚመስላቸውም ተናግራለች፡፡
በኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅትና በዘመቻ ጾታዊ ጥቃት ኢትዮጵያ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚያሳየው፣ ዘንድሮ ለ16 ቀናት እየተከበረ ያለው ፀረ ጥቃት ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹ሰላም ለሴቶች ከጓዳ እስከ አደባባይ›› በሚል መሪ ቃል፤ በአገሪቱ ‹‹ለሴቶች ከጥቃት ነፃ የሆነን ዓለም መፍጠር የእኔም ድርሻ ነው›› በሚል መሪ ቃል መከበሩን ያሳያል፡፡
source:http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment