Saturday, October 12, 2013

“ፕሬዚዳንቱን የደገፍኩት እድሜና ጤናቸውን በማየት ነው”


የፓርላማ ተመራጭ አቶ ግርማ ሰይፉ
አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በእድሜና በጤና ከቀድሞው ፕሬዚዳንት የተሻሉ መሆናቸውን የተናገሩት የአንድነት ፓርቲ አመራርና የፓርላማ ተመራጭ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ገዢውን ፓርቲና ተቃዋሚዎችን በማቀራረብ ለአገራዊ መግባባት አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ በሚል ተስፋ ለፕሬዚዳንቱ ሹመት ሙሉ ድጋፍ እንደሰጡ ገለፁ፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በሹመታቸው ማግስት በጤና እክል ለህክምና ወደ ውጭ አገር መሄዳቸውን አቶ ግርማ ሰይፉ አስታውሰው፤ ጤናቸውን ሲያስታምሙ ምንም ሳይሰሩ ቀርተዋል ብለዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በእድሜም ይሁን በጤና የተሻለ ደረጃ ላይ ስላሉ ይሰራሉ ብለው እንደሚያምኑ አቶ ግርማ ሲገልፁ፤ “አንድን ጉዳይ ድጋፍ የምንሰጠው አልያም ተቃውሞ የምሰነዝረው በምክንያት ነው” ብለዋል፡፡ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ድጋፌን የሰጠሁት፣ ያለ አድልዎ ህዝቡን እንደሚያገለግሉ፣ የተራራቁትን ፓርቲዎች በማቀራረብ ለአገራዊ መግባባት በቀና መንገድ ይሰራሉ በሚል ተስፋ ነው ያሉት አቶ ግርማ፤ በቀናው መንገድ የመስራትና ያለመስራት ምርጫ ግን የፕሬዚዳንቱ ፈንታ ነው ብለዋል፡፡ 
ፕሬዚዳንቱ አሁን ያገኙትን እድል ተጠቅመው በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ስራ ማከናወን ይችላሉ ያሉት አቶ ግርማ፤ “ካድሬ ሆኜ እቀጥላለሁ ካሉ ግን የራሳቸው አሻራ አይኖራቸውም” ብለዋል፡፡ 
አዲሱ ፕሬዚዳንት ባላቸው እድል ከኢህአዴግ ማዕቀፍ በመውጣት ለአገርና ለወገን የሚበጅ ስራ መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ ግርማ፤ በደፈናው የድል ተሳታፊ ነኝ ማለት ተቀባይነት የሌለውና ታሪካዊ ሰው የማያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
Written by  ናፍቆት ዮሴፍ http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment