by ethioadmin
ጥቅምት 19 (ማክሰኞ ረፋድ ላይ) ቀን 2006 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት አዲሱ ፕሬዚዳንት (ዶ/ር) ሙላቱ ተሾመ በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ከ22 ዓመታት
በፊት የጀመረው የዲፕሎማሲ ሥራቸው ቤተ መንግሥት ከገቡም በኋላ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ አምባሳደር ከነበሩበት ቱርክ የስልክ ጥሪ ሲደረግላቸውና ከቱርክ የመጡ እንግዶችም ሊያናግሯቸው ሲጠብቁ ለማየት ተችሏል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊትም የቱርክ ልዑካንን ተቀብለው ማነጋገራቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ የሚያተኩሩት አዲሱ ፕሬዚዳንት፣ ከትምህርት ቤት ያካበቱት ዕውቀትና ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማክተም በኋላ ዓለም የሚመራበት አቅጣጫ ሆኖ ብቅ ከማለቱ ጋር ተዳምሮ፣ የአገሮች ትኩረት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ማጠንጠኑንና መንግሥትም ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ይተነትናሉ፡፡
ለመሆኑ አዲሱ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር የመሆን ሐሳብ ነበራቸው?
‹‹እዚህ ቦታ ላይ ሆኜ ለአገሬ የበለጠ አስተዋጽኦ ላበረክት እችላለሁ ብዬ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስበው ሳላስብ የቀረሁ አይመስለኝም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የሚናገሩ የመንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች፣ በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚው መስክ የነበራቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማስመልከት ፕሬዚዳንት መሆናቸው ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ከዲፕሎማትነት ሥራቸው አኳያ ሲታይ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የተገደቡ ሥራዎችን ብቻ ስለሚያከናውኑ፣ ፕሬዚዳንት መሆን አልነበረባቸውም የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ምን ይላሉ?
‹‹ፕሬዚዳንት ሆኖ አገርን ማገልገል ይቻላል፡፡ አንድ ነገር በግልጽ መናገር የምችለው በዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ቆይቼበታለሁ፡፡ የዛሬ 22 ዓመት ነው ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆኜ ወደ ጃፓን የተላክሁት፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ኢንቨስተሮችን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገው የእኛን ምርቶች ጃፓን ገበያ ውስጥ መሸጥ ነበር፡፡ የጃፓን ቱሪስቶች መጥተው ኢትዮጵያን እንዲያዩ ነበር የምትፈልገው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ ሆኖም በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዳልነበረ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ እንዳልተቻለም ይገልጻሉ፡፡
ከጃፓን ቀጥሎ ወደ ቻይና ያቀኑት ፕሬዚዳንቱ፣ እንቅስቃሴው የተሻለ ወደነበረው ወደ ቻይና መሄዳቸው አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝም ብዙም ሳይጓዙ በጊዜው የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴር በሚባለው ተቋም ምክትል ሚኒስትር ሆነው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ዘርፉን መርተዋል፡፡ ይህም ሹመታቸው ከዲፕሎማሲው ዓለም እንዳላራቃቸው ይናገራሉ፡፡
ከሁሉ በበለጠ በቱርክ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ስኬታማ ሥራ እንደሠሩ እሳቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በአንድ አፍ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንድ ሁነኛ ኢንቨስተር ከመጣ ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው ብለን የምናምን ከሆነ እኔ ራሴ ይዤው እመጣለሁ፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባዔ ነበሩ፡፡ የተከበሩ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ የተከበሩ እንዲህ ነበሩ የሚለውን እንርሳው፡፡ ሥራ ይሠራ ውጤት ይምጣ ከተባለ ያንን ሁሉ ትረሳና መንገድ ታሳያለህ፤›› የሚሉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ አምባሳደር ሳሉ የጀመሯቸውና ያልተቋጩ ሥራዎችን በፕሬዚዳንትነታቸውም እንደሚቀጥሉባቸው አስታውቀዋል፡፡
‹‹በቱርክ ትልቁ ሥራችን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ማንፀባረቅ ነበር፡፡ እዚህ [ቤተ መንግሥት] ከገባሁ በኋላ ሥራ የለም የሚባል ነገር አላየሁም፡፡ በጣም ሥራ ይበዛብኛል፡፡ ቤተ መንግሥት በመሆኔ የቱርክና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትስስር ይዳብራል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በቱሪዝምም በኢንቨስትመንትም የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ሕዝቡም መንግሥትም ፕሬዚዳንታችን ሥራ ሳይፈቱ ኢንቨስትመንት ወደ አገራችን ያመጣሉ የሚል ተስፋ ቢኖራቸው የተሳሳተ አይሆንም፤›› በማለት ፕሬዚዳንት ሙላቱ አዲሱን ሥራቸውን በዲፕሎማሲ ቋንቋ ይገልጹታል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በተለይ ከሪፖርተር ጋር የነበራቸው ቆይታ በመጪው ቅዳሜ በእንግሊዝኛው ዘ ሪፖርተርና በእሑድ የአማርኛው ሪፖርተር ዕትሞች በሰፊ ቃለ ምልልስ ይቀርባል፡፡
Read more here: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment