ይነጋል በላቸው S:http://www.zehabesha.com/amharic/archives/7672
“አውሬ አውሬነቱን አይረሳም” አለ ልበል ተወልደ (ተቦርነ) ስለአንበሣው ቀላቢውን መግደል ሲያወራ አሁን? አዎ፣ ብሏል፡፡ እውነት ነው ፤ አውሬ አውሬነቱን አይረሳም፡፡ ወያኔም ወያኔነቱን አይረሳም – እባብ የትምና መቼም ቢሆን እባብነቱንና የወጣበትን ጉድጓድ እንደማይረሣ ሁሉ፡፡ ወያኔ ፀረ-ኢትዮጵያ ነው፤ ወያኔ ፀረ-አማራ ነው፤ ወያኔ ፀረ-ሃይማኖት ነው፤ ወያኔ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ዴምክራሲ ነው፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያንና ትውፊቶቿን ለማጥፋት የተነሱ የውጭ ኃይላት ብቸኛ ወኪል ነው – ‹የአድኅሮት ኃይላት ተላላኪ፣ የኢምፔሪያሊዝምና የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም አራማጅ ቅጥረኛ› ልበልና የደርግን ዘመን አብዮታዊ ትዝታ ልቀስቅስባችሁ ይሆን? ወያኔ እነኚህን መሰሎቹን የተፈጥሮ ሣይሆን የተጋቦት ባሕርያቱን መቼም አይረሳም – ቢጠግብም – ቢወፍርም -አገርና አካባቢ ቢለውጥም – እርስ በርሱ ቢጣላም – በሎሚ ተራ ተራ አንዱ አንዱን ቢያስርና ቢገርፍም – በማንኛውም ረገድ ወያኔ የተነሣበትን የወያኔነት ጠባይና ምግባሩን አይረሳም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ሰውን ጨምሮ በብዙ እንስሳት የማይታይ አንድ እጅግ አስገራሚ ጠባይ አለው፤ ያም “አህያ ለአህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም” እንዲሉ በወያኔዎች መካከል ደም እስከመቃባት የደረሰ ጠብና ቅራኔ በነሣም እንደቃል ኪዳን ሆኖ ወያኔ ወያኔን ለሌላ አካል አጋልጦ የማይሠጥ መሆኑ ነው፤ ለዚህም ነው አቶ ስዬ አብርሃ ለአሳሪው ለአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ፍራሽ አንጥፎ ከነቤተሰቡ ልቅሶ ተቀምጦ እንደነበር መስማት የቻልነው – መቼም ስዬ እንደክርስቶስ መሓሪ ወይም እንደእግዚአብሔር ሁሉን ታጋሽና ቻይ ሆኖ ነው ብንል ራሱ ስዬ ይታዘበናል – ይህ አስገራሚ ክስተት ከዘረኝነትና ከጎጠኝነትጋር የተያያዘ መሆን አለበት፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ያን ሁሉ ግፍና በደል በኔና በቤተሰቤ ያደረሰብኝ ደብረታቦሬ የ‹ሀገር መሪ› ቢሞት ከሞራልና ከሃይማኖት እንዲሁም ከባህል አንጻር በደስታ ጮቤ መርገጡ ቢቀርብኝ ማቅ መልበሱና ሀዘን መቀመጡ ግን በሟቹ የመቀለድ ያህል እንደሚያስመስልብኝ እገምታለሁና የምሞክረው አይመስለኝም፡፡ የነእንትና ነገር ግን ‹አታሃዛዚቡና› እንደተባለው ነው፡፡ እያልኩ ያለሁት በመለስም ሆነ በሌሎች ወያኔዎች የተበደሉ ወያኔዎች አይዘኑ አይደለም፡፡ ከፈለጉ ቅጥ ባለው መንገድ ማዘን ይችላሉ፤ በይሉኝታቢስነታቸው ቀጥለውበት ትዝብት ውስጥ መግባትን ከቁብ ካልጣፉት ደግሞ ፊታቸውን መንጨትና ሰባትም ዐሥራ አራትም ዓመት ከል መልበስ ይችላሉ፡፡ መጠቆም የፈለግሁት የነሱን ጠብ በውኃ እንደሚፀዳ ተራ ነገር የሚቆጥሩ ሲሆኑ፣ በሌሎች ላይ ቂምና የነገር ቁርሾ ከቋጠሩ ግን ባላጋራዎቻችን ናቸው ብለው የፈረጇቸውን ዕድለቢስ ወገኖች መቀመቅ ካላስገቡ በቀላሉ የማይለቁ እጅግ ሲበዛ መርዘኛ መሆናቸውን ነው፡፡
አለመለከፍ ማለት ቀድሞውን ወያኔን አለመሆን ወይም ወያኔን ሆኖ አለመፈጠር ነው እንጂ አንዴውኑ በወያኔነት ልምሻ ከተኮደኮዱ በኋላ የፈውሱ ነገር አዳጋች ነው – በተለይ እንዳሁኑ ዘመን ጊዜ እየነጎደ በሄደ መጠን የተፈጠሩበትን ዕለት እስከመራገም ለሚያደርስ አሰቃቂ የመጨረሻ ዕጣ ይዳርጋል፡፡ ከዚህ ከወያኔው ዓይነት የዘረኝነት ልክፍት የሚፈወሱና ጤነኛ ሰው የሚሆኑ – ጤነኛ ሆነውም አውቀው አምነውበትም ይሁን ሳያውቁ ተታልለው የበደሉትን ሀገርና ሕዝብ ለመካስ የሚተጉ እጅግ ጥቂቶች ናቸው – ያም እንደገና የመወለድ ያህል መታደል ነው – ለነሱም ለሀገርም፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ የዕንቁ ያህል ውድ ናቸው፤ በቀላሉና የትም አናገኛቸውም፡፡ እናም እንግባባ – ወያኔ ወያኔነትን የትም ሆኖና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለአፍታም አይዘነጋትም፡፡ መዘንጋት ለኅልውናው አደጋ እንደሆነ ያህል ስለሚቆጥረው ይመስለኛል፡፡ አንዲት ማረሚያ ቤት የምትገኝ የወያኔ ወታደር ሰሞኑን በርዕዮት ዓለሙ ላይ ፈጸመቺው የተባለው አስነዋሪ የዘረኝነት ድርጊትም ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው – ለዚህች ደንቆሮ ‹እሥረኛ› ወያኔነት ማለት የገነትም የመንግሥተ ሰማይም ገዢ ነው – ‹እሥር ቤቱና አሣሪዎቹ እኛው እስከሆን ድረስ፣ ገዢዎቹ እኛው እስከሆን ድረስ ይበልጥ እሥረኞች ሌሎች እንጂ እኛ አይደለንም› ብላ ሳታምን አልቀረችም(ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ ሞኝነት የሚነበብበት የወያኔዎች አካሄድ የጆርጅ ኦርዌልን “All animals are equal, but some animals are more equal than the others.” የሚለውን ያስታውሰኛል፡፡) የብዙዎቹ ወያኔዎች መርሆ እነዚህ ብሂሎች ልብ እንድንል ያደርጉናል፡- “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ”፣ “ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ” ፤ “የሥጋ ትል የዘመድ ጥል” ፣ በእንግሊዝኛው ደግሞ “Blood is thicker than water.” ይህ የወያዎች ‹የዋህነት› የሚያሳየን ግን የእግዚአብሔርን መንገድና ትክክለኛውን ማኅበረሰብኣዊ የዕድገት ደረጃን ሣይሆን በዝቅተኛ የንቃትና የዕውቀት ደረጃ የሚገኙ የሌሎች እንስሳትን ነሲባዊ የመሳሳብ ጠባይ ነው፡፡ ሰው ከሰውነት ደረጃ ወርዶ እንዲህ ያለ የደምና የአጥንት ማነፍነፍ ቅሌት ውስጥ ሲገባ ማየት ደግሞ በማኅበረሰብም ይሁን በሀገር ደረጃ ከፍተኛ አለመታደልና የሀፍረት ምንጭም ነው፡፡
የተወልደ በየነ ንግግር እንደዐረብ ጣቢያ ድንገት ጣልቃ ገብቶብኝ በርሱ አባባል ጀመርኩ እንጂ አነሳሴ ቲቪ እያየሁ ሳለ በተጓዳኝ እያነበብኩት በነበረውና አሁን በጨረስኩት አንድ ድንቅ መጣጥፍ ላይ ተመርኩዤ የበኩሌን ጥቂት ለማት ነበረ፡፡ ይህን መጣጥፍ ያገኘሁት በዘሀበሻ ድረ ገጽ ላይ ነው – በፒዲኤፍ የቀረበና ከሰሞነኛ መጣጥፎች ቀልቤን ክፉኛ የሳበ ቆንጆ ጽሑፍ ነው፡፡ ይህ ግሩም ጽሑፍ የቀረበው ከአንድ በስደት ላይ እንደሚገኝ የገለጸ የቀድሞ የመንግሥት ሚዲያ ዘጋቢና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ነው፡፡ ጽሑፉ የሚያትተው ወደፊት መጽሐፍ ሆኖ ይወጣል ከተባለና አንድ የወያኔ ከፍተኛ ባለሥልጣን ይሄው የመንግሥት ሚዲያ ዘጋቢ ከሀገር ሊወጣ ሲል ለሰባት ሰዓታት ያህል በመቅረፀ ድምጽ አጋዥነት ሰጠው ከተባለው የኑዛዜ ቃል ተቀንጭቦ የቀረበ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ርዕሱ “በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ከሚገኝ የልብ ወዳጄ ጋር በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረግሁት ምሥጢራዊ ውይይት” ይላል፡፡ ትንሽ ረዘም ቢልም መነበብ ያለበት ማለፊያ ጽሑፍ ነውና እባካችሁ አንብቡት – ሀገር በጣር ላይ እያለች ለማንበብ መድከም የለብንም፡፡ በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ለሀገር መዋደቅስ አለ አይደል? እየቀነጨብኩ ለፈርጥ ያህል በዚች መጣጥፍ ውስጥ በመጠኑ እንዳልጠቅስላችሁ ጽሑፉን ከፒዲኤፍ ወደወርድ ስለውጠው አንዳንድ ሆሄያት ቅርጻቸው እየተንሻፈፈብኝ ተቸገርኩ፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚተገብራቸውን ሥልቶች ብዙዎቹን ታገኙበታላችሁ፡፡ ወያኔ የቱን ተመርኩዞ የቱን እንደሚያጠፋና ቀጥሎም አንዱን ለማጥፋት የተጠቀመበትን ምርኩዝ ሰባብሮ የትም እንደሚጥል – ባጭሩ ሕወሓት አስብቶ አራጅ መሆኑን ትረዱበታላችሁ›፡፡ በምታምኑት ይሁንባችሁና ግዴላችሁም አንብቡት!
ወያኔ በባሕርይው እንደጅብም፣ እንደውሻም፣ እንደዓሣማም፣ እንደእስስትም፣ እንደእባብም … ነው፡፡ ለወያኔ የባሕርይ መግለጫነት የማይሆኑ ርግብን የመሳሰሉ የዋሃን ፍጡራን ብቻ ናቸው፡፡ በተረፈ ወያኔ ማለት የክፋት ተምሳሌት የሆኑ የተፈጥሮም ይሁኑ ሰው ሠራሽ ነገሮች ውሁድ ሥሪት ነው፡፡ የክፋት አድማሱ ደግሞ ወሰን የለውም፡፡ ድንበር የለሽ ክፋት ደግሞ ድንበርን ተሻግሮ ብዙ ዘመናትን የማጣቀስ ጠባይ አለው፡፡ ለዚህ ነው የክፋት አምባሳደሩ ወያኔም ሞተ ሲሉት እየተነሳ በአፈ ታሪክ ዘጠኝ ነፍስ ያላት መሆኗ እንደሚወራላት ድመት እስካሁኒቷ ቅጽበት ድረስ በአፀደ ሕይወት ሊገኝ የቻለው፡፡
የወያኔ ውሻዊ ባሕርይ፡፡ ውሾች እርስ በርስ ሊዋደዱም ላይዋደዱም ይችላሉ፡፡ ግን ግን እነሱም ልክ እንደብዙዎቹ እንስሳት ዘር መንጣሪና ከ”species”ኣቸው ውጪ ከሌሎች ጋር እምብዝም አይቀላቀሉምና በአደንም ሆነ በሥሮት ወቅት አይለያዩም፡፡ ወያኔዎች ከውሻ የወሰዱት ጠባይ ታዲያ ውሾች በግላቸው የፈለጉትን ያህል ይጣላሉ፣ ይነካከሳሉም እንጂ የውጪ ጠላትና የአደጋ ሥጋት ከተደቀነባቸው ቂጣቸውን ይገጥሙና ያን ጠላት በጋራ ይከላከላሉ፤ በክፉ ቀን በመካከላቸው ንፋስ አይገባም፡፡ አጥንት ላይ የተፋጠጡና የሰገሌን ጦርነት በውሻኛ “version” ሊደግሙት የተዘጋጁ ውሾች ሳይቀሩ ያን ሆድ-ተኮር ጠብ በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አቁመው የመጣባቸውን የጋራ ጠላት በጋራ ይጋፈጣሉ፤ በውነቱ ይህ መልካም ጠባይ ነው፡፡ በወያኔዎች ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረቱና በሰባና ሰማንያ ሚሊዮን በሚገመተው አጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም በሌሎች የፖለቲካና ማኅበረሰብኣዊ ስብስቦች ዘንድ አለመሥራቱ ግን ያሳዝናል፤ ይቆጭማል፡፡ እነሱ ብልጥ ሲሆኑ ሌላው ጅላንፎ ሆኖ እስከወዲያናው በሚመስል ሁኔታ ሲጃጃል መታዘብ ትልቅ ቁጭት ነው፡፡ ከውሻ እንኳን መማር ያቃታቸው ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ወያኔ በቀደዳለቸው የልዩነት መስመር እየተመሙ ለወያኔው ዕድሜ መራዘም ጠንክረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ መቼ ነፍስ እንደሚያውቁና ለከርታታው ‹ሕዝባቸው› መሢሕነታቸውን እንደሚያሳዩ አናውቅም፡፡ ውሻ በበጎም ሆነ በክፉ ብዙ ተጠቃሽ ባሕርያት ቢኖሩትም ለጊዜው ይህ በቂየ ነው፡፡
የወያኔ ጅባዊ ጠባይ፡፡ ጅብ ፈሪ ነው፡- ወያኔም በጣም ፈሪ ነው፡፡ ገደልኩት ብሎ የሚያምነውን ‹ጠላቱን› እንኳን የሚፈራና መቃብር ውስጥም ገብቶ ዐፅምን በምናባዊ የስድብና የምፀት ጅራፍ የሚገርፍ፣ በሙታንም ላይ የሚሣለቅና የሚቀልድ ነው – ወያኔ፡፡ ለምሳሌ አማራንና ኦርቶዶክስን ገድሎ እንደቀበራቸው በወያኔዊ መድረኮች ካላንዳች ሀፍረትና ይሉኝታ እየተደሰኮረ ነው፡፡ ግዴለም ሞቱ እንበል፡፡ በሕይወት ያሉ እየመሰለው ታዲያን በባነነ ቁጥር በሚናገራቸው የዕብሪት ቃላቱና በሚያከናውናቸው ፀረ-ሕዝብ ተግባራቱ ለትዝብት እንደተዳረገ አለ ፡፡ ፍርሀት በራስ የመተማመን ችሎታን ያሳጣል፤ ፍርሀት ቤቱን የሠራበት ሰው እንደመለስ ተሳዳቢና አሽሟጣጭ ይሆናል፡፡ ፍርሀት ያሸነፉትን ጠላት እንዳላሸነፉት በማስቆጠር ቀን በእውን ሌት በውን እያስባተተና እያስቃዠ ወንጀለኛና ኃጢኣተኛ ያደርጋል፡፡ የወያኔ ወንጀል እየተቆለለ ሄዶ ለፍርድ አስቸጋሪ እስኪሆንበት ድረስ ፈጣሪን እያስጨነቀ ያለው እንግዲህ ከዚህ መሠረታዊ ምክንያት በመነጨ መሆን አለበት፡፡ እንዲያ ባይሆንስ ቁናው ከሞላ ሰንብቷል፡፡
ጅብ ሆዳም ነው፡፡ የጅብ ሆድ ደግሞ የሚመርጠው የለም፡፡ ያገኘውን እየሰለቀጠ ወደጎሬው ይገባል፡፡ የነጋበት ጅብ በተለይ አይጣል ነው፡፡ ወያኔ እንደዛሬው ሳይነጋበትም ሆነ እንደዱሮው በጊዜ ያገኘውን ሁሉ ማግበስበስ መነሻና መድረሻ ዋና ጠባዩ ነው፡፡ ወያኔ አይጠግብም – እምብርት የለውምና፡፡ ከመሰል ሰብኣዊ ጅቦች ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ራቁቷን እያስቀራት ያለ ወያኔ ነው፡፡ ጅብ ሆዳም ብቻ አይደለም፡፡ የብዙ ብልሹ ምግባራት ተምሳሌት ነው፡፡ ለአብነት እርስ በርሱ አይተማመንም፡፡ ከዚያም የተነሣ ሲሄድ እንኳን ፊትና ኋላ ሆኖ ሳይሆን ጎን ለጎን ሆኖ ነው ይባላል፤ በተለይ የቆሰለ ጅብ በመንጋው ውስጥ ካለ በጣም ካልተጠነቀቀ በስተቀር ከአህያ ያልተናነሰ ዕድል እንደሚገጥመው ይነገራል – በቁሙ ነው አሉ እሚዘረጥጡት፡፡ ወያኔም እንደዚሁ ነው፡፡ አይተማመኑም፤ እርስ በርስ ይበላላሉ፡፡ ተባልተው ተባልተው መጨረሻቸው ደርሷል እየተባለ ነው አሁን፡፡ ለሰው ማን እንዲህ ሹክ እንደሚለው አላውቅም፤ ግን ‹መዥገሩ ወያኔ በደም አብጦና በደም ሰክሮ ሊፈርጥና ሊበታተን ነው› እየተባለ በየቦታው ሲወራ እሰማለሁ – ወፍ ትሆናለች እንዲህ እያለች ምሥጢር እያወጣች ያለች – እንዳፏ ያድርግልን፡፡ ለመሆኑ ግና – መለስ ብለን መለስን ስናስታውስ የወዲ ዜናዊ ሠይፍ ያልቀላው ትላልቅና ትናንሽ ወያኔ አለ ወይ? እንዴ፣ ያልተቆረጠመ ሰው እኮ የለም፤ የመለስ ነዲድና ፍላጻ ሞኛሞኙንና ቅን ታዛዡን ብቻ መርጦ ትቷል፡፡ በልዩ ወርቃማ ዕድል ከዐይኑ የተሠወሩበት ጥቂት ብልጣብልጦችና አድርባዮች ለዘር እንዲተርፉ የመለስ ውቃቢ አምላክ ምሯቸው እንደሆነ እንጂ መለስ የፈጀው ሕዝብ እኮ በውነቱ ከግምት በላይ ነው፤ መለስ ዜናዊ? ኧሯ! በጊዜ መሰብሰቡ በጄ(ን/-ኣቸው(?)) እንጂ ከርሱ ሾተል ማን ሊተርፍ ይቻለው ነበር? በተለይ እሱ የወያኔ ባለሥልጣን ከሆነበት የብረት ትግሉ የመጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ በዚህ ሰውዬ ሥውርና ግልጽ ትዕዛዝ እንዲሁም የሽርና የተንኮል ሤራ በመርዝና በጥይት ብዙ የወያኔ ታጋይ እንዳለቀ ለጉዳዩ ቅርበት ባላቸው ሃቀኛ ወገኖች የተጻፉ ድርሳናት ይመሰክራሉ – የገብረ መድኅን አርአያ ጽሑፎችን ያነቧል፡፡ ይሄ ሁሉ እየታወቀ ግን መለስን እስከማምለክ ተደርሷል – ምክንያቱም መለስን መቃወምና መንቀፍ ማለት ከጥቅምና ከጋርዮሽ ዘውጋዊ ቁርኝት ጋር ይጣረሳላ! ምክንያቱም መለስን መቃወም ማለት አሁን የተደረሰበትን የአንድ ብሔር ሸፋፋና ቅጥየለሽ “የበላይነት” ሊያሳጣ እንደሚችል ይታመናላ! ድንቄም የበላይነት! የበላይ የሆኑትስ እየተበደሉና እየተረገጡ የሚገኙት በርካታ ሚሊዮን ወገኖች ናቸው፡፡ የበላይ የሆኑትስ እየተራቡና እየተጠሙ፣ እየታረዙና እየታመሙ፣ እየተጋዙና እየተገደሉ፣ በእሥርና በስደት አሰቃቂ ሕይወትም መከራቸውን እየበሉ ያሉት ምሥኪኖች ናቸው፡፡ የበላይ የሆኑትስ በገዛ ሀገራቸው እንደሦስተኛና አራተኛ ዜጋ ተቆጥረው የማንኛውም የኢኮኖሚና የፖለቲካ መብታቸው ሳይከበርላቸው እንደከብት እንዲኖሩ የተገደዱ ትግሬውን ጨምሮ የየትኛውም ዘውግ አባላት ናቸው፡፡ የበላይ የሆኑትስ ለኅሊናቸው ያደሩና ሀገራቸውን ከወያኔ ጋር ተባብረው ያልሸጡ የሁሉም ዘውግ አባላት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ማን የበላይ ማን ደግሞ የበታች እንደሆነ በጊዜ ሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ በጮማ ግሣትና በውስኪ ብስናት ሕዝብ ላይ እያቀረሹ መኖር የበላይነት መገለጫ ሳይሆን የአውሬነትና የእንስሳነት ጠባይ ማሳያ ነው፡፡ ኤዲያ … በቃኝ እባክሽ፤ አናጋሪዎች!
No comments:
Post a Comment