‹‹እኝህ ሰውዬ የሁለቱን አገሮች ዕርቅ ለማሳካት ሞራላዊ ብቃት የላቸውም፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ሳስበው ደም መለገስ እንጂ ከኤርትራ የምናተርፈው ምንም ነገር የለም፡፡
ኤርትራ መቼም ሰላማዊ ጎረቤት መሆን አትችልም፡፡ ቅኝ ገዥዎችና የሁለቱ አገሮች መሪዎች ታሪክን ንደዋል፡፡ ያንን ለማስተካከል ሌላ ምዕተ ዓመት ይፈጃል፡፡ ለተረጋጋች ኢትዮጵያ ኤርትራ ባለችበት መደንዘዝዋ ጥሩ ዕድል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ዕርቅ በመፈጸም ዳግም ታሪካዊ ስህተት እንዲፈጽም ዕድል መሰጠት የለበትም፡፡ አሁንም ውስጥ ያሉት አልተውንም፡፡ ለራሱ ለመንግሥትም አደጋ ናቸው፡፡ መጠንቀቅን ቢረዳ መልካም ነው፡፡ የሻዕቢያ የስለላ መዋቅር አደጋ ነው፡፡ ያን አደጋ መከላከል የሚቻለው አሁን ባለን የባላንጣነት ጉርብትና ሒደት ውስጥ ነው፡፡››
ይኼ አስተያየት በሪፖርተር ድረ ገጽ ከተሰጡት በርካታ ተመሳሳይ አስተያየቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ኸርማን ሐንክ ኮኸን፣ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ለማስታረቅ ‹‹ጊዜው አሁን ነው›› በሚል ለተመድ ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ ከተዘገበ በኋላ የወጣ ነው፡፡
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊንና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አቀራርበው ለማነጋገር ያልተሳካ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ በአሜሪካ መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ተሰሚነት ካላቸው ግለሰቦች መካከል መሆናቸውም ይነገርላቸዋል፡፡ ኸርማን ኮኸን ባቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ ላይ የተለያዩና እርስ በርስ የሚቃረኑ አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ ለመሆኑ በመፍትሔ ሐሳባቸው ውስጥ ያካተቱት ድምዳሜ ምንድነው?
የሁለቱም አገሮች የድንበር ውዝግብ አጣብቂኝ ያበቃ ዘንድና ዕርቅ እንዲያደርጉ የሚል ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንድትቀበልና የባድመን መሬት እንድታስረክብ ይጠይቃሉ፡፡ በመቀጠልም የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ አጠቃላይና ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ፣ የዕርቅ ሒደቱም ከሁሉቱም አገሮች ጋር መልካም ግንኙነቱን ጠብቆ በቆየ አንድ አውሮፓዊ አገር ተነሳሽነት እንዲወሰድ የሚል ነው፡፡
የኸርማን ኮኸን የዕርቅ ሐሳብ መነሻ
የኢትዮጵያና የኤርትራን የድንበር ግጭት ተከትሎ በተደረገው ጦርነት ከሁለቱም አገሮች ከ70 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉ አይዘነጋም፡፡ ሁለቱም አገሮች በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በመሆናቸው ቀላል ግምት የማይሰጠው ንብረትና ሀብትም ወድሟል፡፡ በርካታ ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉም ምክንያት ሆኗል፡፡ ጦርነቱ ያበቃው ሁለቱም አገሮች በፈረሙት ‹‹ይግባኝ አልባ›› የሆነ የአልጀርስ ሽምግልና ስምምነት ሲሆን፣ ይህንን እንዲተገብር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያላገኘውን ፍርድ በመስጠት ተበትኗል፡፡ በዚህ ምክንያት ሁለቱ አገሮች ከአሥር ዓመት በላይ ሰላምም ጦርነትም አልባ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሁለቱም መንግሥታት መካከል አልፎ አልፎ አነስተኛ መተናኮስ ቢስተዋልም፣ ቀጥተኛና በሙሉ ልብ ጦርነት ሊሰኝ የሚችለው ክስተት አላጋጠመም፡፡ ሆኖም በሁለቱም አገሮች መካከል ሰላም ባለመኖሩ፣ በሕዝቦች መካከል ሊደረግ የሚችል ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትብብር የሚታሰብ አልሆነም፡፡ ከዚያም ባሻገር በክልሉ የውክልና ጦርነት ሊሰኝ የሚችል በተለይ በሶማሊያ ተስተውሏል፡፡ በመሆኑ የሁለቱም አገሮች ሰላም አለመሆን ሶማሊያን ጨምሮ በአጠቃላይ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይነግስ ምክንያት ሆኗል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የፀጥታ ሁኔታ እርሱ በርስ የተቆላለፈ መሆኑን በመተንተን፡፡
በዚህም ምክንያት መንግሥትን ጨምሮ በርካቶች በሁለቱም መንግሥታት መካከል ሰላም ለማስጀመር ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ፡፡ አብዛኞቹ የዕርቅ ጥረቶች ውስጥ ለውስጥ ተሞክረው የሚከሽፉ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የዕርቅ ሐሳቦቹን አጠቃላይ ይዘትና አንድምታዎች ለመተንተን አስቸጋሪ ቢያደርጉትም፣ ‹‹ባድመን ሰጥቶ የአሰብ ወደብን መቀበልን›› ጭምር የዕርቅ ሐሳብ ሆኖ መቅረቡ በስፋት እየተነገረ ነበር፡፡ በዚያው ልክ የዕርቅ ሐሳቦቹ ለምን ተቀባይነት እንደማያገኙ ለመተንተን ለብዙዎች አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
የኸርማን ኮኸን የዕርቅ ሐሳብ ከቀደሙት ጥረቶች በተለየ ሁኔታ በግልጽና በሚዲያ ይፋ የሆነ በመሆኑ፣ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የዕርቅ ሐሳቡ ከዚህ በፊት ከቀረቡት ወይም በመንግሥት ተቀባይነት ያላገኘው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ተገልብጦ የመጣ ቢሆንም፣ በሦስት ውጫዊ ምክንያቶች የተለየ ቅኝት ያለው ይመስላል፡፡ አንደኛው ሐሳቡ በቀረበበት ወቅት ‹‹የዕርቅ ጊዜው አሁን ነው›› መባሉ፣ ሁለተኛ ዕርቅ እንዲደረግ የቀረበበት የመነሻ ሐሳብና የዕርቁ ውጤትና አንድምታ ናቸው፡፡ የዕርቁን ሐሳብ የበለጠ አነጋጋሪ ያደረገው ምክንያትም ይኼው ይመስላል፡፡
‹‹ኤርትራን መታደግ ጊዜው አሁን ነው›› በሚለው ርዕስ በወጣለት ጹሑፍ ‹‹የዕርቅ ጊዜው አሁን ነው›› የተባለበት ምክንያት፣ አሁንም ሁለቱም ሕዝቦች ‹‹በሰላምና በጦርነት አልባ›› ምክንያት ግንኙነታቸው ከዚህ በላይ ተቋርጦ መቆየት እንደሌለበት ያስገነዝባል፡፡ የሁለቱም መንግሥታት መሪዎች በተለያዩ ወቅቶች ዕርቅ እንደሚፈልጉ በሚዲያ መናገራቸውን እንደመነሻ ቀርቧል፡፡
ለዚህም ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ ለአልጄዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹አስመራ ድረስ ሄጄ ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ›› ማለታቸውን ልብ ይሏል፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ በቅርቡ ከራሳቸው የመንግሥት ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አገራቸው ያለኢትዮጵያ ሕልውና የሌላት መሆኗን አመላካች ነገሮች መናገራቸው ነው፡፡ በአገራቸው የሚገኙት ፋብሪካዎችና የልማት ድርጀቶች በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት ሥራ እየሠሩ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የአሰብ ወደብ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ጠቀሜታ እንደሌለውና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አስገንብተው ለኢትዮጵያ ማቅረብ ከዕቅዳቸው መካከል መሆኑን መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡ ሁለቱም አገሮች በመካከላቸው በተቋረጠው ግንኙነት ደስተኛ አለመሆናቸውንና ለመታረቅ ዝግጁነት እንዳላቸው አመላካች መሆኑ ለኸርማን ኮኸን መነሻም ይኼው ነው፡፡ ‹‹ሁኔታው አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ምንም ምክንያትም የለም፤›› ይላሉ፡፡
ለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ምላሽ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የቀረበው ባለአምስት ገጽ ‹‹የሰጥቶ መቀበል›› መርህ አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወት ባይኖሩም፣ በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት የባድመን ግዛት አሳልፎ ለመስጠት በመንግሥት በኩል ዝግጅት ስለመኖሩ እስካሁን አንድም ምልክት የለም፡፡
ሁለተኛው ኤርትራ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንድትገለል ምክንያት የሆነው በሶማሊያ የመሸገውን አልሸባብ ትረዳለች የሚለው ሪፖርት ሲሆን፣ በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ሁለቴ እንዲጣልባት ምክንያት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ ለእዚህ አሸባሪ ቡድን ዕርዳታ ስለማድረጓ ምንም ማስረጃ አልተገኘም በማለት ኸርማን ኮኸን ይከራከራሉ፡፡ እንዲያውም በፀጥታው ምክር ቤት የተጣለባት ማዕቀብ በአሜሪካ የግል ተነሳሽነት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የዕርቁ ውጤትም ሁለቱም ሕዝቦች በሰላም እንዲኖሩና እንዲተባበሩ መሆኑን ውጫዊ ጉዳዮችን አስፍረዋል፡፡ አንደኛው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኤርትራ የሚፈጸሙ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማስቆም በር ይከፍታል የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያና የኤርትራ ዕርቅ በአሜሪካና በኤርትራ መንግሥታት መካከል ወታደራዊ ትብብር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ይላሉ፡፡ በዚያ መንገድ በአካባቢው ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ይረዳል የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡
ኸርማን ኮኸን በአሜሪካ መንግሥት ተቀባይነት አላቸው ከሚባሉት መካከል ቢሆኑም፣ አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ በመፍትሔነት ያቀረቡት ሐሳብ ግን ሌሎች ምሁራን ከሚያቀርቡት ሐሳብ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎችም አቋም ይኼው ነው፡፡
‹‹ቲንክ አፍሪካ ፕሬስ›› የተባለ ዕውቅ ሚዲያ ባለፈው ዓመት ‹‹በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዴት ሊመጣ ይችላል?›› በሚል ያቀረበው ጽሑፍ ጉዳዩን በጥልቀት የሚመለከት ነው፡፡ ሳሊህ ኑር የተባሉ በአስና ብሩክ ዩኒቨርሲቲ (DAAD - ጀርመን) ዲሞክራቲክ ገቨርናንስ በመማር ላይ የሚገኙ ኤርትራዊ ሲሆኑ፣ ቀደም ሲል በአስመራ ዩኒቨርሲት መምህር የነበሩ ናቸው፡፡ ድርድር መጀመር ካለበት የቀውሱ እውነተኛ ምክንያት መፈተሽ አለበት ከሚል መነሻ መፍትሔ የሚጠቁሙት ተመራማሪው፣ ከወዲሁ በአልጄርሱ ስምምነት መሠረት በድንበር ኮሚሽኑ የተሰጠው ውሳኔ ለምን አልተሳካም በሚል መጀመር አለበት ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት በመሠረቱ የችግሩን ምንጭ የማይፈትሽ፣ የችግሩን አንድ ገጽ (የድንበር ግጭት) ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ የችግሩን ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ያላካተተ ከመሆኑም ባሻገር፣ የመጨረሻና ይግባኝ የሌለው መባሉ መቼም መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ ውሳኔው በውስጡ እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ ፍሬ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ለትግበራ ፍፁም የሚመች አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያልቅ ዕልባት መስጠት ስህተት መሆኑን፣ እንዲህ ዓይነት ውጥንቅጡ የወጣ መንስዔ ያላቸው ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት በይበልጥ በፖለቲካዊ ድርድር መሆን ያስረዳሉ፡፡
በብዙ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን አድናቆት ያገኙት ጸሐፊው መፍትሔ ሲጠቁሙም፣ የሁለቱ አገሮች የዕርቅ ሐሳብ አሁንም የድንበር ኮሚሽኑ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናውን መሠረት ይህንን ውሳኔ ሳይለቅ መደረግ እንዳለበት ሁሉ፣ ማናቸውም የዕርቅ ሙከራዎች ከድንበር ግጭቱ በላይ አጠቃላይ የሕዝቦችን ችግር የሚመለከቱ መሆን እንዳለባቸው ይጠቁማሉ፡፡ በምሳሌነት ያነሱት አንድ ጉዳይም ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ሁሌም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ቅሬታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ማግኘት የምትችልበት ወይም በሊዝ በሥርዓት መጠቀም የምትችልበትን መንገድ ማፈላለግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ሦስተኛ ቀጣይነት ያለው ሰላም ይፈጠር ዘንድ በሁለቱም ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ታሪካዊ ቅሬታ በሃይማኖት መሪዎች ጭምር ዕርቅ በመፍጠር፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመንና ቅሬታ መወገድ እንዳለበት ይጠይቃሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የችግሩ አካል ቢሆኑም በኸርማን ኮኸን ጽሑፍ አይገኙም፡፡
ከኸርማን ኮኸን ጽሑፍ በአንድ ሳምንት ቀድሞ የወጣ ‹‹Ethiopian and Eritrea Brothers at War no More›› (የኢትዮጵያና ኤርትራ የወንድማማቾች ጦርነት ሲያበቃ) የሚል ፍቺ ያለው ጽሑፍም እጀግ ጠቃሚ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል ‹‹ወንድማማቾት በጦርነት ላይ….›› የሚለውን በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ከተጻፉት ግንባር ቀደም የሆነው መጽሐፍ ደራሲና በጀርከንስ ኮሌጅ የሰላምና የግጭት ፕሮፌሰር የሆኑት ኬቲል ትሮንቨል ከሌላ ኢትዮጵያ ወጣት በመሆን በጋራ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡ በጋራ ጽሑፋን ያቀረበው ጎይቶም ገብረልኡል የኢንተርናሽናል ሕግና ፖሊሲ ተቋም አማካሪ ቀደም ሲል በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት አስተማሪ የነበረ ነው፡፡ አጥኚዎቹ የአሥመራ መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ለኢትዮጵያ መንግሥት ሥጋት እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በአስመራ ያሉት ሁኔታዎች ኤርትራ መንግሥት አልባ የመሆን ዕድሏ እንደያጎሉ ያስረዳሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥት እያጋጠመው ካለው የስደት ቀውስና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ‹‹በመትረፍ ሁኔታ›› (Survival Mood) ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሁለቱ ወንድማማቾች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው አለመተማመን፣ መቃቃርና የግጭት ስሜት ሥጋት የገባቸው እነዚህ ምሁራን፣ በሁለቱም አገሮች ያሉት አዳዲስ ክስተቶች ግን ሁኔታውን ሊለውጡት ይችላሉ ብለዋል፡፡
‹‹ዘለዓለማዊ›› (Omnipresent) ነዋሪ የሚመስሉ ያሉዋቸውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቆየ ግንኙነትና ፋክክር በተፈጠረው ችግር ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑኑ ገልጸው፣ ከሁለቱ መሪዎች በኋላ አዲስ ግንኙነት ሊፈጠር ይችላል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡
ባድመን ለመስዋዕትነት?
ኸርማን ኮኸን መፍትሔ ባሉት ሐሳባቸው ከላይ የተጠቆሙት ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ግምት ውስጥ ያስገቡ አይመስልም፡፡ ጎይቶም ገብረልኡል ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የቀድሞው አሜሪካዊ ዲፕሎማትና የመፍትሔ ሐሳብ አንድም ጠባብ ምልከታ ነው ወይም በሁለቱ አገሮች ያሉትን አዳዲስ ክስተቶች ግምት ያስገባ አይመስልም፡፡ የኸርማን ኮኸን ግምት የሁለቱ አገሮች ችግር በቀላሉ በዕርቅ ሊያልቅ ይችላል የሚል ነው፡፡ ተመራማሪው ጎይቶም እንደሚገልጸው ግን፣ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት አዲስ ገጽታ የሚይዘው ከሁለቱም ጠንካራ ተፎካካሪ መሪዎች በኋላ ነው፡፡ እንደ ጎይቶም ዕምነት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሥልጣን ላይ እስካሉ ድርስ ዕርቅ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በአገር ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ያጋጠማቸው ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ችግር መፍታት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ ውጪ የሚገፉበትን በር መዝጋት ነው፡፡ የዲሞክራሲ፣ የሥርዓት፣ የሕገ መንግሥትና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ስለሚነሱባቸው የሚያሳብቡበት ብቸኛ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ችግር መሆኑ ይናገራል፡፡ ኸርማን ኮኸንም ይህንኑ አስታውሰዋል፡፡ ከዕርቁ በኋላ የምዕራብ መንግሥታት በኤርትራ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
በኤርትራ ጉዳይ የድንበር ቀውስና ኢትዮጵያን ባህር አልባ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስንና ኢሕአዴግን ተጠያቂ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በሕወሐት ውስጥ በ1993 ዓ.ም. ለተፈጠረው መሰንጠቅ ዋና ምክንያት እንደሆነም ይወሳል፡፡ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሚካኤል ወልደ ማርያም የተባሉ ምሁር፣ ‹‹Badme Border Dispute Why Ethiopia won’t Back on Eritrea Border›› በሚለው ጥናታዊ ጹሑፋቸው፣ የባድመ ችግር በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ጓዶቻቸው ጋር የተገናኘ መሆኑን ጠቁመው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ትሮንቮል እና ወጣት ጎይቶምም በድኅረ መለስና ድኅረ ኢሳያስ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ወደ ቀደሞው መመለስ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ቅርፅም ይይዛል በማለት ይተነብያሉ፡፡
በመግቢያው የተጠቀሰው በሪፖርተር ድረ ገጽ ከተሰጡ ከአርባ በላይ አስተያየቶች የኸርማን ኮኸንን ሐሳብ የሚቃወሙ ኢትዮጵያን የሚበዙ ሲሆን፣ በተለያዩ በማኅበራዊ ድረ ገጾችም የመፍትሔ ሐሳቡን የሚያጣጥሉ ኢትዮጵያዊያን ተስተውለዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ መቀጠል እንዳለባት፣ ካልሆነ ከኤርትራ ጋር የሚደረግ ዕርቅም ሆነ ጦርነት የባህር በር ጥያቄን ያካተተ መሆን እንዳለበት ከተጻፉ በርካታ አስተያየቶች መገንዘብ ተችሏል፡፡
የተመድ አጣሪ ቡድን በኤርትራ ላይ ያቀረባቸው ሪፖርቶችን እውነታነት ያጣጣሉት ኸርማን ኮኸን ሥጋት፣ ኤርትራ መንግሥት አልባ የምትሆንበት ጊዜ በመቃረቡ የሽብርተኝነት መናኸርያ እንዳትሆን ነው፡፡ የዕርቅ ሐሳቡም የሁለቱን አገሮች ችግር በስፋት የማይመለከትና ምንም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይተቻሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በምን ዓይነት መንገድ ሐሳቡን እንዳይቀበለው በማሳሰብ፡፡
‹‹ከኢትዮጵያ ጋር መኖር ባርነት ነው ብለው ከተለዩ አሁን ጊዜው የዕርቅ ሲባል ሊስማሙ ነው ወይ? ወይስ ያለ ከኢትዮጵያ በመለየት ያገኙት ነፃነት ብቻውን ዳቦ መሆን ስላልቻለ በዕርቅ ሽፋን ዳቦ ለማግኘት? እውነት እውነቱን ስንነጋገር ኢትዮጵያ ያለ ኤርትራ መኖር ትችላለች፤ ኤርትራ ግን አይቻላትም፤›› በማለት አንድ አስተያየት ሰጪ ገልጿል፡፡
ኸርማን ኮኸን ኤርትራ እ.ኤ.አ. ከ2009 ወዲህ ሽብርተኛውን አልሸባብ ረድታ አታውቅም ብለው ቢከራከሩም፣ ተመድ ግን ከዚያ በኋላ ሁለት ጊዜ ማዕቀብ መጣሉ እንዴት ተረሳቸው የሚሉም አሉ፡፡ ስለዚህ ኸርማን ኮኸን ምን እየፈለጉ ነው የሚለው ትልቁ ጥያቄ ሆኗል፡፡
No comments:
Post a Comment