Tuesday, December 24, 2013

ሚሊየነሩ ኒቆዲሞስ ዜናዊ (ከእየሩሳሌም አርአያ)


ኒቆዲሞስ ዜናዊ የአቶ መለስ ዜናዊ ወንድም ነው። ከወ/ሮ አለማሽ ገ/ልኡልና ከአቶ ዜናዊ አስረሳኸኝ የተወለዱ ወንድማማቾች ናቸው።
ኒቆዲሞስ በደርግ ስርአት በክብሪት ፋብሪካ ተቀጥሮ በተራ ሰራተኝነት ይሰራ ነበር። የአካል ጉዳተኛ (አንድ እግሩ) የሆነው ኒቆዲሞስ ከተራ ወዝአደርነት ወጥቶ ሚሊየነር ለመሆን የበቃው ደርግ ወድቆ ሕወሐት/ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ነበር። የፋብሪካ ስራውን በግንቦት 1983ዓ.ም ማግስት የለቀቀው የአቶ መለስ ወንድም ኒቆዲሞስ ከአሜሪካ በ25ሺህ ዶላር የተገዛች አዲስ አውቶማቲክ ማርሽ አውቶሞቢል እንዲይዝ ተደረገ።

ተራ ወዛደር የነበረ ሰው 25ሺህ ዶላር የሚያወጣ መኪና ሊገዛበት የሚችል የገንዘብ አቅም እንደሌለው ግልፅ ቢሆንም ነገር ግን ይህን ያክል የገንዘብ መጠን በማውጣት ለኒቆዲሞስ የተበረከተለት ስጦታ ወንድሙ አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት ሕወሐት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነበር። ይህም ብቻ አይደለም፤ ኒቆዲሞስ አካል ጉዳተኛ ነው በሚል ሰበብ አውቶሞቢሉ የጉምሩክ ቀረጥ ሳይከፈልበት ነበር አገር ውስጥ የገባው። ይህን ጉዳይ በተመለከተ “ወጋህታ” የተባለች በትግርኛ ቋንቋ በአገር ውስጥ ትታተም የነበረች የነፃው ፕሬስ ጋዜጣ ከጉምሩክ ለኒቆዲሞስ ዜናዊ ያለቀረጥ መኪናው እንዲገባ የተሰጠውን፣ በስሙ ተፅፎ ከነመኪናው ሻንሲ ቁጥር ጭምር የተገለፀበትን ደረሰኝ ማስረጃ በማውጣት ጋዜጣዋ አጋልጣለች። ከዜና ዘገባው ጋር በተያያዘ በወቅቱ በተለያዩ ጋዜጦችና ሌሎች ወገኖች ከተነሱት አስተያየት አዘል ጥያቄዎች ተከታዩ ዋናው ነበር፤ « ..ኒቆዲሞስ ዜናዊ ያለቀረጥ አውቶሞቢል እንዲገባለት የተደረገው ከበላይ አካል በተላለፈ ቀጭን ትእዛዝ ነው። የገንዘብ ምንጩ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እንደሆኑ ግልፅ ነው። ከመኪናው ግዢ እስከ ጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ፍቃድ ድረስ ሙስና ተፈፅሟል። ኒቆዲሞስ ይህን ህገ-ወጥ ጥቅም እንዲያገኝ ሲደረግ የአገሪቱ መሪ አቶ መለስ ወንድም በመሆኑ ነው። ስለዚህም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አቶ መለስ ከሙስናው ጋር በተያያዘ ሊጠየቁ ግድ ነው። ለምሳሌ በሙስና እንዲከሰሱ ከተደረጉት ባለስልጣናት አንዱ አቶ ስዬ አብርሃ የቀረበባቸው ክስ በቂ ማስረጃ ወይም ማመሳከሪያ ነው። አቶ ስዬ ለወንድማቸው ምህረተአብ አብርሃ ሰባት መኪኖች ያለቀረጥ እንዲገቡ አድርገዋል የሚለው ክስ ይጠቀሳል። አንድ መኪና ሆነ ሰባት አሊያም ሰባት መቶ..ቀረጥ እስካልተከፈለባቸው ድረስ ሙስና ለመሆኑ አያጠያይቅም። ስለዚህም የኒቆዲሞስ ጉዳይ ሙስና መሆኑ ግልፅ
ነው። ከተፈፀመው ቀረጥ ያለመክፈል ክስ ጋር ኒቆዲሞስና ወንድሙ አቶ መለስ በሙስና ሊከሰሱ ይገባ ነበር። » የሚሉ ነጥቦች ነበሩ ከተለያዩ ወገኖች ይነሱ የነበረው። ይህ ጉዳይ በተለይ በስፋት አነጋጋሪ ሆኖ የነበረው በዘጠናዎቹ የመጀመሪያ አመታት ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ተከታዩ ነው።
ኒቆዲሞስ ዜናዊ ከተራ ወዝአድርነት ወጥቶ በአንድ ግዜ ሚሊየነር የሆነበት ሚስጥሩ በ1988 ዓ.ም አንድ የኤርትራና ጣልያን ዘር ያለው ግለሰብ ከሮም አዲስ አበባ ይመጣል። ከዚያም ከኒቆዲሞስ ዜናዊ በጋራ « ጃክሮስ ኢትዮጲያ » የተባለ ድርጅት ያቋቁማሉ። ኒቆዲሞስ የጃክሮስ ግማሽ (50%) ባለድርሻ ሆኖ ነበር ድርጅቱ የተመሰረተው። “ጃክሮስ” በተቋቋመ ማግስት የመንግስት ሚዲያ የሆኑትን የኢትዮጲያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ እንዲሁም ፋና ራዲዮ በማስታወቂያ ተቆጣጠረው። በተጨማሪ የአማረ አረጋዊ « ሪፖርተር » ጋዜጣ ማስታወቂያ በተጋነነ መልኩ ከማውጣት ባለፈ ስለ ድርጅቱ (ጃክሮስ) ሰፊ የዜና ዘገባና ትንታኔ በመስራት ተከታታይ ሽፋን መስጠት ያዘ።
በጋዜጣውና በመንግስት መገናኛ ይቀርቡ የነበሩት ማስታወቂያዎችና ዘገባዎች ፥ « ..ጃክሮስ ኢትዮጲያ, በአገራችን የመጀመሪያው
የመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚያካሂድ፤ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቪላዎችን በመገንባት ለደንበኞቹ በአጭር ግዜ ውስጥ ሰርቶ የሚያስረክብ ነው፤ ለግንባታ ከሚጠቀማቸው ቁሳ-ቁሶች መካከል በተለይ ለቪላው ማሳማሪያ የሚጠቀማቸው ከውጭ አገር የመጡና ዘመናዊ ናቸው፤ እንደ ደንበኛው ፍላጎትና ምርጫ የሚገነባው በቂ የዋስትና ሽፋን በድርጅቱ የሚሰጠው ሲሆን፣ ጃክሮስን የተለየ የሚያደርገው የሚገነቡት ቪላዎች ስታንዳርዳቸውን የጠበቁና የውጭ አገር ዘመናዊ ቪላዎች አይነት መሆናቸው ጭምር ነው። ደንበኛው ሙሉ ክፍያ የሚከፍል ከሆነ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ መኖሪያውን አጠናቆ ያስረክባል፤ ከደንበኛው ጋር በሚደረግ ስምምነት ክፍያው ተፈፃሚ ይሆናል፤ ይህ ማለት የረጅም አመት ክፍያ ድርጅቱ ይሰጣል።…» የሚሉት በተጋነነ መልክ ይቀርቡ ከነበሩት ይጠቀሳሉ።
ድርጅቱ እንደ ሽፋን የተጠቀመበትና የተጠቀሱት ሚዲያዎች ያራግቡ የነበረበት አንድ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። በ1988ዓ.ም የአትላንታ ኦሎምፒክ የሚካሄድበት አመት ነበር። እነ ሃይሌ ገ/ስላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦሎምፒክ የሚሳተፉበት፣ እነ ፋጡማ ሮባና ደራርቱ ቱሉ የተካተቱበት ጭምር ነበር። ሁሉም ኢትዮጲያዊ ማለት ይቻላል ከወራቶች ቀደም ብሎ ውድድሩን በጉጉት እንዲጠብቅ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። “ጃክሮስ” ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ኢላማ አድርጎ የተነሳው የአንጋፋው አትሌት ሻለቃ ዋሚ ቢራቱን ቤት በነፃ እገነባለሁ በሚል ነበር። በቀድሞ ወረዳ 12 ቀበሌ 07 የሚገኘውን የዋሚ ቢራቱ መኖሪያ በሁለት ወር ውስጥ ሰርቶ እንደጨረሰ ተናገረ። ቀደም ሲል የነበረውን የዋሚ ቤት በማደስ የሰራውና በከፍተኛ ደረጃ የተራገበለት መኖሪያ በቲቪ መስኮት የታየውና ተጨባጩ እውነታ ለየቅል ነበሩ።
ለቤቱ ግንባታ ተብሎ ዙሪያውን የዋለው ለተለያዩ ቁሳቁሶች ማሸጊያነት (ለምሳሌ ከውጭ የሚገቡ ፍሪጆችና ቴፕ..ወዘተ ጉዳት እንዳይገጥማቸው ከውስጥ በማሸጊያነት ) የሚውለው ፎም ነበር። ከዚያ በቀለም እንዲያሸበርቅ ከተደረገ በኋላ « 2 ሚሊዮን ብር
በማውጣት ጃክሮስ ለዋሚ ቢራቱ ቤት ገንብቶ አስረከበ..» ተብሎ በጋዜጣውና በሚዲያ አስነገረ። አንጋፋው አትሌት በወቅቱ ከአሜሪካ ለመጣውና ቀበሌ 11 ለሚኖረው እስክንድር አሰፋ ስለቤቱ ሲናገር በሃዘን ጭምር ነበር፤ « የበፊቱ መኖሪያዬ ይሻለኝ ነበር። እንኳን 2 ሚሊዮን ብር 1ሺህ ብር አልወጣበትም። እኔን መነገጃ ማድረጋቸው ለምን እንደሆነ አልገባኝም።» ነበር ያለው ዋሚ። በእርግጥም እነኒቆዲሞስ በዋሚ ነግደዋል።
ከአሜሪካ የመጡ መኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ጃክሮስን አምነው 70ሚሊዮን አስረከቡ። ሌሎች ወገኖችም ቀለጡ። አንድ አመት ቢጠብቁ ምንም ነገር የለም። ከአሜሪካ የመጡ ወገኖች ከብዙ መንከራተት በኋላ የደረሰባቸውን በደል በኢ.ቲ.ቪ “አይናችን”ፕሮግራም ቀርበው « ለአመታት ሰሃን አጥበን፣ ደም ተፍተን ሰርተን ያጠራቀምነውን ገንዘብ በአደባባይ ተዘረፍን። ህግና መንግስት ባለበት አገር እንዴት እንዘረፋለን?..መንግስት ይፍረደን!.» በማለት በእንባ እየተራጩ አቤቱታቸውን አሰሙ። እነ ኒቆዲሞስ ከህብረት ኢንሹራንስ ጋር የዋስትና ውል አለን ብለው ያሉትም በጭራሽ ከተገለፀው ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው የህብረት ኢንሹራንስ ዋና ሃላፊ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በወቅቱ አጋለጡ። ኤርትራዊው የጃክሮስ ባለድርሻ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በወረዳ 12 ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰር ተደረገ።
የሚገርመው ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል መሆኑ እየታወቀ፣ ጉዳዩ በማእከላዊ ምርመራ መያዝ ሲገባው ወይም የጃክሮስ ቢሮ ይገኝበት በነበረው ቦሌ አካባቢ ባለ ፖሊስ ጣቢያ መታየት ሲገባው…ከድርጊቱ ጋር ግንኙነት በሌለው ወረዳ 12 የፖሊስ ጣቢያ ጉዳዩ መያዙና መታሰሩ እንቆቅልሽ ነበር። ሶስት ቀን ብቻ ከታሰረ በኋላ ፍ/ቤት ሳይቀርብ “በ2ሺህ ብር ዋስ” ተፈታ። በተፈታ ማግስት በቦሌ እንዲወጣ ተደረገ። ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው ኒቆዲሞስ ነበር። የተዘረፉት ወገኖች በድጋሚ ወደ ኢ.ቲ.ቪ ቢሄዱም መስተናገድ አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነበር።
የዘረፋው ጉዳይ በነፃው ፕሬስ በየግዜው ቢነሳም ሰሚ ግን አልነበረም። ነሐሴ 1993ዓ.ም አቶ መለስ ዜናዊ ከጋዜጠኛ ሴኮቱሬ ስለጉዳዩ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ አስገራሚ ነበር። ሴኮ « ከወንድሞ ጋር በተያያዘ የሚነሳ ነገር አለ፤ ስለጉዳዩ የሚሉት ነገር ይኖራል?» ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ « በመጀመሪያ ደረጃ ወንድሜን ያገኘሁት ከአስር አመት በኋላ በእናታችን የቀብር ስነስርአት ላይ ነው። አዲስ አበባ እንደገባን ካገኘሁት በኋላ አግኝቼው አላውቅም። የተባለውን ጉዳይ በተመለከተ እነደሰማሁ ከዚህ ተግባር እንዲታቀብ ነግሬው ነበር» አሉ። የአቶ መለስ ምላሽ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነበር፤ “አግኝቼው አላውቅም” ካሉ በኋላ መልሰው ደግሞ “ከዚህ ተግባር እንዲታቀብ ነግሬው ነበር” አሉ። ሌላው ነጥብ ወንድማቸው ኒቆዲሞስ በዘረፋ ወንጀል ተሰማርቶ እንደነበር ማመናቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል።
ኒቆዲሞስ ዜናዊ በአቋራጭ ዘርፎ ሚሊየነር ሆነ። እጅግ አምባገነን ባህርይ የተጠናወተው ሰው ነው። ማን እንዳስታጠቀው የማይታወቅ ማካሮቭ ሽጉጥ አለው። በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው “ሃረግ” መዝናኛ ያዘወትር ነበር። በሴተኛ አዳሪዎች ላይ ሽጉጥ እየመዘዘ ፍዳቸውን ያሳይ ነበር። ማንም አይጠይቀውም።
ሲጠቃለል፥ ከጥቂት ወራት በፊት በመለስ ዜናዊ ቤተሰብ ዙሪያ በኢ.ቲ.ቪ አንድ ፕሮግራም ተሰርቶ ነበር። «ጠላ ሻጭ» ወዘተ ተብለው የቀረቡት ከአቶ መለስ ጋር በአባት የሚገናኙ ናቸው። ኒቆዲሞስና መለስ ግን የአንድ እናትና አባት ልጆች ናቸው። ስለሚሊየነሩ ኒቆዲሞስ ምንም የተባለ ነገር የለም። ለምን እሱ በፕሮግራሙ አልተካተተም?...ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። ዘርፎ ሃብታም እንደሆነ በማስረጃ ስለተጋለጠና ህብረተሰቡ ጉዳዩን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው።
via: ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com

No comments:

Post a Comment