የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አብዲ ሞሀመድ ኦማር ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጎሳው አባላት የተነሳውን ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ የሶማሊ ክልል አዲሱ ምክር ቤት ድጋፍ እንደሰጣቸው ታውቋል።
ከክልሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ አብዲ የየረር ጎሳ አባላትን አልሸባብ እየተባለ ከሚጠራው የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አድርገው በማቅረብ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ፈቃድ ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል።
ውሳኔው መተላለፉን ተከትሎ የየረር ባሬ ጎሳ አባላት የአለም ህዝብ እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል።
በቅርቡ ልዩ ሚሊሺያ እየተባለ የሚጠራው ታጣቂ ሃይል በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በወሰደው እርምጃ ህጻናት ተማሪዎችን ጨምሮ 48 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ሰዎች ገልጸዋል። በቅርቡ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች በታጣቂዎች በመገደላቸው የሟቾች ቁጥር 50 መድረሱን የጎሳ መሪዎቹ ይገልጻሉ።
የአገር ሽማግሌዎቹ በልዩ ሚሊሺያው የተገደሉ የ48 ሰዎች ስም ዝርዝር ያለበትን ደብዳቤ ለጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጉባኤና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማስገባታቸው ይታወቃል። ወደ 17 የሚጠጉ የአገር ሽማግሌዎች አቤቱታቸውን አቅርበው ሲመለሱ በልዩ ሚሊሺያው ታስረዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት በጎሳ አባላቱ ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ ግልጽ አላደረጉም። በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን የህዝብ ግንኙነት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
Source: Ethsat
No comments:
Post a Comment