የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ሪፖርት ሳያዳምጥ መለሰ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጠር ረገድ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ እንቅስቃሴውን ዘንድሮም አጠናክሮ ቀጥሎታል፡፡
ባለፈው ዓርብ ለምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ሊያቀርቡ የተገኙ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችን በመመለስ ሚኒስትሩ እንዲቀርቡ አዟል፡፡
ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ለማቅረብ ተገኝተው የነበሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተለያዩ ዳይሬክተሮች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የቋሚው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልጅዓለም ወልዴ ሪፖርቱን ለማቅረብ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ባለመሆናቸው ቅር በመሰኘት፣ በምክር ቤቱ አዳራሽ ተገኝተው የነበሩትን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዳይሬክተሮች እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ለፓርላማው ተገቢውን ክብር እየሰጠ አለመሆኑን በወቅቱ የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን በመግለጽ በቀጣዩ ሰኞ ሚኒስትሮቹ ቀርበው ሪፖርቱን እንዲያቀርቡ አዘዋል፡፡
በዚህም መሠረት ባለፈው ሰኞ ማለዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁ በምክር ቤቱ በመገኘት ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ከሚኒስቴሩ ይፈልግ የነበረው ሪፖርት በአርብቶ አደሮች አካባቢ ስላለው ወቅታዊ የጤና ሽፋን የሚመለከት ነው፡፡
በተለያዩ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በተለይም በአፋር ክልል የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ብቃት ማነስ ላይ ሚኒስቴሩ በአግባቡ መሥራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
Read more here: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment