ጥቅምት ፳፯(ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጸረ ሽብር ግብረሀይል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላላፈው መልእክት አልሸባብና በኤርትራ የሚደገፉ ሀይሎች በመላው አገሪቱ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጁ መሆኑን አስተማማኝ መረጃ ደርሶኛል ብሎአል። ዜጎች እራሳቸውን ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጿል።
ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ፍተሻዎች ሲደረጉ የሰነበቱ ሲሆን፣ የትናንቱ ማስጠንቀቂያም ይህን ተከትሎ የተሰጠ ነው። መንግስት በኤርትራ የሚደገፉ የሽብር ሀይሎች ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጅተዋል ቢልም እነዚህን ሀይሎች ከመዘርዝር ተቆጥቧል። መንግስት በኤርትራ የሚደፉ ሀይሎች ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው አላሳወቀም። መንግስት በኤርትራ የሚደገፉ አሸባሪዎች በማለት የፈረጃቸው ድርጅቶች ግንቦት7፣ ኦነግና ኦብነግ ናቸው። መግለጫውን ተከትሎ ከትናንት ምሽት ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ኬላዎች ላይ ፍተሻ በመካሄድ ላይ ነው። መንግስት የሽብር ጥቃት አደጋ ተደቅኖብኛል ቢልም ከኢትዮጵያውያን በኩል የሚቀርበው ምላሽ ተቃራኒውን እየሆነ ነው። በማህበራዊ ድረገጾች የሚወጡ እንዲሁም ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች ፣ ” መንግስት ራሱ ፈርቶ ህዝቡን እያስፈራራ መሆኑን” የሚያመለክቱ ናቸው። ብዙ አስተያየት ሰጪዎች የመንግስትን ማስጠንቀቂያ አይቀበሉትም። አንዳንዶች ዜጎች ራሳቸውን ከመንግስት የተቀነባባረ የሽብር ጥቃት መጠበቅ እንዳለባቸው ይመክራሉ።የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትናንት ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት የ2006 ዋነኛ አጀንዳው ኢትዮጵያን ከሽብር ጥቃት መከላከል መሆኑን አሳውቋል።
No comments:
Post a Comment