ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን በጋራ የተዘጋጀው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አስነሳ፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዳማ (ናዝሬት) በተካሄደው ስብሰባ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች፣
ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ያለባት ጥቅም በግልጽ ሊነደገግ ይገባል የሚል አቋም ይዘው ተከራክረዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊው ድንጋጌ በአዋጅ ተደግፎ ሳይወጣ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሊሆን አይገባም በማለት፣ የኦሕዴድና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡
ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ንዑስ ቁጥር አምስት ላይ ባስቀመጠው ድንጋጌ ‹‹የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ፣ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅበታል፤›› ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ የኦሮሚያን ጥቅም ለማስከበር ዝርዝር ጉዳዮች በሕግ እንሚወሰኑ ያስረዳል፡፡
የአመራሮቹ መከራከሪያ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕግ ማዕቀፍ ተተንትኖ፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልታገኝ የምትችላቸው ጥቅማ ጥቅሞች ሊረጋገጡ ይገባል የሚል ነው፡፡
አንዳንድ የኦሕዴድ አመራሮች ከዚህ መከራከሪያ ባሻገር በጥልቀት በመሄድ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ጥቅም እንኳ ባታገኝ፣ መጎዳት ግን እንደሌለባት ተከራክረዋል፡፡ ለዚህ መከራከሪያ በምክንያትነት የቀረበው ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የፈሳሽ ቆሻሻና የደረቅ ቆሻሻ ጉዳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የውኃ ምንጮች በሙሉ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ ከውኃ ምንጮቿ መካከል ለገዳዲና ገፈርሳ ግድቦች፣ እንዲሁም የአቃቂ ከርሰ ምድር ውኃ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የኢሕአዴግ ካድሬዎች እንደሚናገሩት ከእነዚህ የውኃ ምንጮች አዲስ አበባ ውኃ በመሳብ ስትጠቀም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በንፁህ የመጠጥ ውኃ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው አዲስ አበባ የቆሻሻ መጣያዋን በኦሮሚያ ክልል አካባቢ በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ትንሹና ትልቁ የአቃቂ ወንዞች ሙሉ በሙሉ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆስፒታሎችና መኖሪያ ቤቶች ተበክለው ወደ ኦሮሚያ ክልል ይፈሳሉ፡፡ በኦሮሚያ በተለይም በልዩ ዞኑ ደቡብ ምሥራቅ አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በተጨማሪ፣ ለሰዎችና ለእንስሳት አደገኛ የበሽታ ጠንቅ ናቸው በማለት ባለሙያዎች በተለያዩ ጽሑፎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የተሰጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሚያወጡት ቆሻሻ ነዋሪዎች የሚጠቀሙበት ወንዝ ውስጥ እየገባ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ በዘለለም ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሕዴድ አመራሮች በድንበር አከላል ጥርጣሬ ከማሳደራቸውም በላይ፣ በማስተር ፕላኑ አማካይነት ልዩ ዞኑን ከአዲስ አበባ ጋር የማቀላቀል ፍላጎት አለ የሚል አስተያየት አላቸው፡፡
የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የተዘጋጀው የጋራ ማስተር ፕላን የተጠቀሱትን ችግሮች ከመፍታቱም በላይ፣ ለሁለቱም ክልሎች የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኛል በሚል ለማግባባት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ማግባቢያውን አልተቀበሉትም፡፡ ‹‹ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሲሆን ኦሮሚያ ተጠቃሚ ስለመሆንዋ ምን ማረጋገጫ አለ?›› በማለት ጥርጣሬያቸውን በማጉላት ጉዳዩን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
በ1995 ዓ.ም. የተዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስተር ፕላን በ2005 ዓ.ም. የመጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ማስተር ፕላን አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ በቅርቡ እንደ አዲስ የተዋቀረውን የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲያቅፍ ተደርጓል፡፡
በልዩ ዞኑ ስድስት ከተሞችና ስምንት የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆኑ፣ እነዚህ ከተሞችና የገጠር ወረዳዎች ከአዲስ አበባ ጋር የተቀናጀ ካርታ ተሠርቶላቸዋል፡፡ የተሠራላቸው ማስተር ፕላን የተጠናቀቀ በመሆኑ ተግባር ላይ የሚውለው ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና የልዩ ዞኑ ምክር ቤት ሲያፀድቁት ብቻ ነው፡፡
ማስተር ፕላኑ ከመፅደቁ በፊት የአዲስ አበባና የልዩ ዞኑ አመራሮች በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ ይዘው ኅብረተሰቡን እንዲያወያዩ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ሰሞኑን እነዚህን አመራሮች ለማሠልጠን የተያዙት ፕሮግራሞች የተሳኩ እንዳልሆኑ ስብሰባውን የተከታተሉ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አዳማ ላይ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በተካሄደው የአሠልጣኞች ሥልጠና ላይ በተለይ ከኦሮሚያ አመራሮች ጉዳዩ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በልዩ ዞኑ ጉዳይ ላይ የሚወስነው መላው የኦሮሚያ ሕዝብ መሆን አለበት፣ ይህ ጉዳይ የማንነት ጉዳይ ነው የሚሉ አስተያየቶች በወቅቱ ተሰንዝረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ የተወከሉ አመራሮች ግን ጉዳዩን ለማለሳለስ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ እነዚህ አመራሮች ይህ ማስተር ፕላን የተዘጋጀው ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ ከአገሪቱ ዕድገት አንፃር፣ ከሕዝቡ ቁጥር ዕድገት፣ አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ልዩ የሆነ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ለራሷና ለአቅራቢያ ከተሞች ያስፈልጋል በሚል መነሻነት መሆኑ ተዘርዝሯል፡፡
ከዚህ ባሻገርም የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኦሮሚያ ክልል መሥሪያ ቤቶች፣ ከፍተኛ የባህል ማዕከላት መሥሪያ የሚሆን ቦታ በነፃ ማቅረቡ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን አባባሉ ያላረካቸው አመራሮች ጉዳዩ የአመለካከት ችግር ተደርጐ እንዳይወሰድባቸው በመጥቀስ፣ ይህ በቂና አሳማኝ መረጃ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በተሰጣቸው ማብራሪያ ባይረኩም፣ ስብሰባውን የመሩ ከፍተኛ አመራሮች አለመግባባቱን በማስወገድ ኅብረተሰቡን ማወያየት የግድ መሆኑን በመግልጽ የስብሰባውን አቅጣጫ ለማስተካከል ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ስብሰባውን የመሩ ከፍተኛ አመራሮች ተጭነው ለማሳመን ቢሞክሩም፣ ከስብሰባው በኋላ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ካድሬዎች አልተዋጠላቸውም፡፡
የኦሮሚያ ክልልን ጥቅማ ጥቅሞች ለመደንገግ ከአምስት ዓመታት በፊት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዓመቱ ስለሚሠሩ ሥራዎችና ስለሚወጡ ሕጎች በገለጹበት ወቅት፣ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ስለምታገኘው ጥቅማ ጥቅም ሕግ እንደሚወጣ ገልጸው ነበር፡፡ ነገር ግን አዋጁ በዚያኑ ዓመት ካለመውጣቱም ባሻገር፣ እስካሁን ድረስም አልወጣም፡፡
ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሲደረግ አዲስ አበባና ልዩ ዞኑ በጠቅላላ 1.1 ሚሊዮን ሔክታር ስፋት ይኖረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ 54 ሺሕ ሔክታር መሬት ነው ያረፈችው፡፡
No comments:
Post a Comment