Saturday, June 22, 2013

የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር ከትንበያው በመቀነሱ ሳቢያ የመረጃ ፍተሻ ተካሄደ

 ለቁጥሩ መቀነስ በተሰጠው ምክንያት ኮሚሽኑ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል ተብሏል ለመረጃ ፍተሻው 61 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ሆኗል
የአማራ ክልል ህዝብ ብዛት ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከትንበያው በጣም ዝቅ ብሎ በመገኘቱ የኢንተርሴንሳል ሥነ ህዝብ ናሙና ጥናትና የመረጃ ፍተሻ ተካሄደ፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረትም በህዝብ ቁጥሩ ላይ መሻሻሎች መታየታቸው ይፋ ሆኗል፡፡ ሪፖርቱ ይፋ ባደረገው የዕድገት ምጣኔ ውጤት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የትምህርት ሚኒስትርና የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ሊቀመንበር በሆኑት በአቶ ደመቀ መኮንን የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የ1999/2000 ሶስተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ህዳር 25ቀን2001 ዓ.ም ይፋ ሲደረግ፣ የአማራ ክልል ህዝብ ብዛት ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከትንበያው በጣም ዝቅ ማለቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል፡፡

በዚህ ምክንያትም ተጨማሪ ፍተሻ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ጽ/ቤት በሰኔ2001 ዓ.ም ለምክር ቤቱ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ምክር ቤቱ የኢንተርሴንሳል ጥናት እንዲካሄድ የወሰነ ሲሆን፡፡ በዚህ መሠረትም ከመንግስት ካዝና በ2004 በጀት ዓመት ብር 64.416.182 ብር፣ ከተባበሩት መንግስታት የሥነህዝብ ፈንድ ደግሞ 9.116.555.34 ብር በአጠቃላይ ብር 73.532.737.34 ተመደበ፡፡ ከዚሁ ገንዘብ ውስጥም 60.837.254.12 ብር ወጪ ተደርጎ የኢንተርሴንሳል ጥናቱና የመረጃ ፍተሻው ተካሄደ ሲሆን ውጤቱም ይፋ ሆኗል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት ያደመጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያሉ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
የቀድሞው ሪፖርት ለምክር ቤቱ በቀረበበት ወቅት፣ የአማራ ክልል ህዝብ ከትንበያው እጅግ ዝቅ ለማለቱ ምክንያት ነው ተብሎ የቀረበው ኤችአይቪ ኤድስ በከፍተኛ ሁኔታ የክልሉን ህዝቦች ማጥቃቱ መሆኑ የተገለፀው አግባብነት የሌለውና የክልሉን ህዝብ ስሜት የነካ በመሆኑ ኃላፊዎቹ እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል የሚል አስተያየት ከምክር ቤት አባላት ተሰንዝሯል፡፡ የክልሉ ህዝብ የዕድገት ምጣኔ እንደሆነ ተገልፆ በቀረበው ሪፖርት ላይም አባላቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የህዝቡ አመታዊ የዕድገት ምጣኔ ከ1.73 ወደ 2.3 እንዲያድግ የተደረገ ቢሆንም አሁንም ይህ ቁጥር እንኳንስ በለጋ ዕድሜ ጋብቻን ፈጽሞ በርካታ ልጆች በሚወለዱበት በአማራው ክልል ይቅርና አደጉ በሚባሉ አገራትም ሊሆንና ሊታሰብ የማይችል ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ አውሮፓ ባሉ ታላላቅ የአለማችን አገራት ውስጥ የሌለ የዕድገት ምጣኔ አምጥቶ በአማራው ክልል ላይ መደፍደፍ አግባብነት ያለው ተግባር ነው ብለን አናምንም ሲሉም አባላቱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ በምክር ቤቱ የሚገኙት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ (የመድረክ) ተወካዩ አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ 2.99 ሚሊዮን በሚለው የአዲስ አበባ ህዝብ ብዛትና 2.1 በመቶ የዕድገት ምጣኔው ላይ ቅሬታቸውን ለምክር ቤቱ አሰምተዋል፡፡ በምክር ቤት አባላቱ ለቀረቡት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የትምህርት ሚኒስትርና የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ሰብሳቢው አቶ ደመቀ መኮንን፤ የቀድሞ ሪፖርት በድጋሚ እንዲታይና የመረጃ ማጣሪያ እንዲደረግ በተሰጠው ውሣኔ መሠረት ማጣሪያው ተሠርቶ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ገልፀው፤ ይህ መረጃ በጥቅም ላይ መዋል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ በበኩላቸው፤ የቀድሞው ሪፖርት ስህተት የነበረው ከትንበያው ላይ መሆኑን ጠቁመው የኢንተርሴንሳል ጥናቱና በመረጃ ማጣራት ሥራው የተገኘው ውጤት ይፋ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በ2004 ዓ.ም በተደረገው የኢንተርሴንሳል ጥናትና የመረጃ ማጣራት ሂደትም የአማራ ክልል ህዝብ ብዛት 19.2 ሚሊዮን መድረሱን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ብዛትም 2.99 ሚሊዮን መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ምክር ቤቱ በኮሚሽኑ የቀረበውን የ2004 የኢንተርሴንሳል ሥነህዝብ ጥናት እንዲፀድቅ አድርጓል፡፡

No comments:

Post a Comment